Popular Posts

Thursday, October 17, 2019

የንቀት መድሃኒት



እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ለሌሎች ሰዎች በረከት የሚሆንን ነገር አስቀምጧል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሄር የእኛን ህይወታችንን በረከት ያስቀመጠው በሌላው ሰው ውስጥ ነው፡፡ ሌላውን ሰው መናቅ የእግዚአብሄርን ስጦታ መናቅ ነው፡፡ ሌላውን ሰው መናቅ የእግዚአብሄርን ስጦታ መጣል ነው፡፡ ሌላውን ሰው መናቅ ከእግዚአብሄር በረከት ጋር መተላለፍ ነው፡፡
እውነት ነው ሁላችንም የህይወት ደረጃ አለን፡፡ ሁላችንም የምናከብረውና የምንንቀው ነገር አለ፡፡ በተለምዶ አብረን ለመስራት የምንመርጠውና የማንመርጠው ሰው አለ፡፡ ለጓደኝነት የምንመርጠውና የማንመረጥው ሰው ሊኖር ግድ ነው፡፡ ነገር ግን የምንመርጥበት መመዘኛ መዛባት ምርጫችንን ከትእቢት የመነጨ ንቀት ያደርገዋል፡፡  
ሁላችንም በተለያየ ጊዜ ሌሎችን ለመናቅ እንፈተናለን፡፡ በተለይ ድካም ያየንበትን ሰው ይህ ሰው ለምንም አይጠቅምም አይረባም በማለት ለመናቅ በእጅጉ እንፈተናለን፡፡ ሰውን አይረባም አይጠቅምም ብሎ መናቅ እና ዝቅ ዝቅ አድርጎ ማየት ግን ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ በሰው ላይ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ መቁረጥ ግን የክፉ እግዚአብሄራዊ ምዘና አይደለም፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ እንደ እነርሱ የሰው ልጆች የሆኑትን ሰዎች ዝቅ ዝቅ አድርገው ለሚያዩና ለሚንቁ ሰዎች ብርቱ ማስጠንቀቂያ አለው፡፡ ነው፡፡
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። የማቴዎስ ወንጌል 5፡22
አንተ ከሌላው እንድትለይ እና እንዳትናቅ ያደረገህ እግዚአብሄር ነው፡፡ ከእግዚአብሄር በተቀበልከው ነገር መልሰውህ እንዳንተው በእግዚአብሄር የተፈጠረውን ሰው ለመናቅ መጠቀም አግባብ አይደለም፡፡
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡7
ንቀት ከትእቢት ይመጣል፡፡ ንቀት ያለን ነገር ባለቤቱ እኛ እንደሆንን በስህተት ከማሰብ ይመጣል፡፡
እርሱን እንድትንቀው ያደረገው የሃጢያት ፍላጎት በአንተም ውስጥ አለ፡፡ እርሱን እንደዚህ እንድትንቀርው ያደረገውን የሃጢያት ፍላጎት ይዘህ እንደአንተው የተፈጠረውን ሰው መናቅ አለማስተዋል ነው፡፡
ንቀት በክፉ ከመፍርድ ይመጣል፡፡ ንቀት ማሰብ ከሚገባው አልፎ ራስን ከፍ አድርጎ ከማየት ይመጣል፡፡ ንቀት ማሰብ ከሚገባው አልፎ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ከማየት ይመጣል፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የያዕቆብ መልእክት 2፡1
ሰው እግዚአብሄር እንዴት እንደሚያከብረው እንደ አይኑ ብሌን እንደሚጠነቀቅለት ሲያውቅ እግዚአብሄር ሌላውንም ሰው እንደሚያከብረው ስለሚያውቅ ሌላውምን ለመናቅ አይደፍርም፡፡
ሰው እግዚአብሄር እንዴት እንደወደደው ሲረዳ እግዚአብሄር ደግሞ ሁሉንም ስለሚወድ ከእግዚአብሄር ጋር ተባብሮ ሰዎችን ሁሉ ይወዳል ያከብራል እንጂ ማንንም አይንቅም፡፡ ሰዎችን የሚንቅ ሰው እግዚአብሄር እንዴት እንደወደደው በደንብ ያልተረዳ ሰው ነው፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም። 1 የዮሐንስ መልእክት 3፡1
ሰው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል እንደተፈጠረ ሲረዳ ፣ ራሱን ሲያከብርና ሲወድ ሌላውን ያከብራል ማንንም አይንቅም፡፡
ሰውን የሚንቅ ሰው መናቅ የጀመረው ራሱን ነው፡፡ ሰውን የሚንቅ ሰው ለራሱ የሚገባ ፍቅርና አክብሮት የለውም፡፡ ሰውን የሚንቅ ሰው ራሱን እንደሚገባ አያከብርም አይወድም፡፡ ሰውን የሚያከብር ሰው ራሱን እንደሚያከብር ማረጋገጫው ነው፡፡

ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። የማቴዎስ ወንጌል 22፡39
ሰው ሰው ቢደክም እና ቢወድቅ እንኳን አንተ እንዳትወድቅ ያደረገህ ያው እግዚአብሄር የወደቀው እንዲነሳ ያደርገዋል፡፡
አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፡4
ንቀት በራስ ካለመተማመን ይመጣል፡፡ እውነተኛ የከበረ ሰው ሰውን በማክበር ይታወቃል፡፡ እውነተኛ ከአጉል ፉክክር የዳነ ሰው ሌላውን በማክበር ይታወቃል፡፡ ሰው ትልቅነቱ የሚታወቀው በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ታላቅነትን በማየት ችሎታው ነው፡፡ ሰው ትልቅነቱ የሚታወቀው ከድካም አልፎ ብርታት በማየት ችሎታው ነው፡፡ ሰው ታላቅነቱ የሚያወቀው በትንሹ ሰው ድካም ላይ ሳይሆን በሰው ጥንካሬው ላይ በማተኮር ችሎታው ነው፡፡
ሰውን የሚንቅ ሰው መረዳት የጎደለው ሰው ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር የሰውን ልጅን በመልኩና በአምሳሉ እንደፈጠረውና ምን ያህል እንደሚወደው ከእግዚአብሄር ቃል እየተረዳ ሲሄድ ሌላውቅን ሰው ለመናቅ አቅም ያነሰዋል፡፡ ሰው መረዳቱ ሲጨምርና ነገሮችን እንደ እግዚአብሄር መረዳት ሲጀምር የሚንቀውን እየተወ የሚያከብረውን እያበዛ ይሄዳል፡፡ 
እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም እርሱም በማስተዋል ብርታት ኃያል ነው። መጽሐፈ ኢዮብ 36፡5
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ንቀት #ትህትና #ትእቢት #ጥንካሬ #ብርታት #ቃል #ህይወት #አገልግሎት #አምልኮ #ፀሎት #ጥሪ #ተመልክተን #መቃጠል #መቀጣጠል #ክብር #አገልግሎት #መዋረድ #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment