Popular Posts

Friday, October 11, 2019

ሞገስ በስራ ላይ



እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣሉ። ትንቢተ ኢሳይያስ 55፡5
እግዚአብሄር እርሱን በምንፈልግ በእያንዳንዳችን ህይወት በትጋት እየሰራ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሲሰራ ብዙ ጊዜ አይጮኽም፡፡ እግዚአብሄር በዝምታ እና ውስጥ ውስጡን ሰራ ማለት እግዚአብሄር እየሰራ አያደለም ማለት አይደለም፡፡
እግዚአብሄር በዝምታ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ ሞገስን በመስጠት መንገዳችንን ማቅናት ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያለውን አላማውን ለመፈፀም ሞገስን ይሰጠናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ መዝሙረ ዳዊት 84፡11
በእያንዳንዱ የህይወታችን ክፍል የእግዚአብሄርን የሞገሱን ስራ መጠበቅ ይገባናል፡፡ ሁሉም የህይወታችን ነገር ተሰልቶ የሚታወቅ መሆን የለበትም፡፡ በጎደለው ነገር የእግዚአብሄርን ሞገስ ተስፋ የምናደርግ መሆን አለብን፡፡ በህይወታችን የእግዚአብሄርን ከተፈጥሮ በላይ የሆነን የሞገስን አሰራር መጠበቅ አለብን፡፡
የእግዚአብሄርን የሞገስ እርዳታ ለመረዳት እና በእያንዳንዱ ቀን የእግዚአብሄርንም የሞገስ አሰራር ለመጠባበቅ ሞገስ ምን እንደሆነና በምን እንደሚገለጥ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
1.      ሞገስ የማይገባንን ተቀባይነትን ይሰጣል
ሰዎች ስለአንድ ነገር የሚቀበሉት ሰው አለ የማይቀበሉት ሰው አለ፡፡ ሰዎች ሰውን የሚቀበሉበት የተለያየ መመዘኛ አላቸው፡፡ ሰው የመሆን አንዱ ስጦታ በነፃ ፈቃድ መምረጥ መቻሉ ነው፡፡ ሰው የመሆን አንዱ ስጦታ የሚመርጠውና የማይመርጠው ነገር መኖሩ ነው፡፡  
ሰዎች ሰዎችን የሚቀበሉበትን መመዘኛዎች ሁሉ አሟልተን ሰዎች ከተቀበሉን ምንም አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሰዎችን የሚቀበሉበትን መሰረታዊ የብቃት ደረጃ ሳናሟላ ሰዎች ከተቀበሉን ይህ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ የእግዚአብሄር አሰራር ነው ብለን መቀበል እንችላለን፡፡  
ህይወት ፍፁም አይደለም፡፡ የሚያስፈልገውን መመዘኛ ሁሉ ሁል ጊዜ ማሟላት አንችልም፡፡ ህይወትን ፍፁም የሚያደርገው የእግዚአብሄር አሰራር ነው፡፡ የጎደለንን የሚሞላውና የእግዚአብሄር ሞገስ ነው፡፡
አንድ ሴት ለአቅመ ሄዋን ከደረሰች ጀምሮ ብዙ ወንዶች ወደ እርስዋ ይሳባሉ፡፡ እርስዋም ወደ ብዙ ወንዶች ልትሳብ ትችላች፡፡ ነገር ግን ወደ እርስዋ የተሳቡትን እርስዋም ወደ እነርሱ የተሳበቻቸውን ወንዶች ለማግባት አትወስንም፡፡ በህይወትዋ ዘመን እንዲመራትና እንዲንከባከባት በፊትዋ ሞገስን የሚያገኘው አንድ ወንድ ብቻ ነው፡፡ ባሌ ይሆናለ ብላ የምትወስነው ወንድ ከሌሎቹ ወንዶች በምን እንደተለየ ብዙም ላይገባት ትችላለች ነገር ግን እንዲሁ በፊቷ ሞገስን ያገኛል፡፡ 
 አስቴርም በሚያዩአት ሁሉ ዓይን ሞገስ አግኝታ ነበርና። መጽሐፈ አስቴር 2፡15
ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። መጽሐፈ ምሳሌ 1822
2.     በእግዚአብሄር ሞገስ ምክኒያት ሰዎች እምቢ ያሉትንና የከለከሉትን ይፈቅዱልናል
ሰዎች በተለምዶ የሚከለክሉትን ነገር ለእኛ ከፈቀዱልን የእግዚአብሄር ሞገስ ከእኛ ጋር እየሰራ እንደሆነ ማረጋገጫው ነው፡፡
በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ። በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው፤ ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ። መጽሐፈ ነህምያ 2፡8-9
የእግዚአብሄር ሞገስ ከእኛ ጋር ሲሰራ ሰዎች ሃሳባችንን ለማስፈፀም ከተለመደው የተለየ በትጋት ይሰራሉ፡፡
የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም፦ እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ። መጽሐፈ ነህምያ 2፡18
3.     እግዚአብሄር በእኛ ላይ ካስቀመጠው ሞገስ የተነሳ ሰዎች ካለምክንያት ይወዱናል
እውነት ነው ሰዎች እኛን የሚወዱበትን ምክኒያት በግልፅ ሊያውቁና ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ካለ ምክኒያት ሲወዱ ይህ ሰው እንደሁ ደስ ይለኛል ሲሉ የእግዚአብሄር ሞገስ አንዱ መገለጫው ነው፡፡ ሰዎች ወደ ሌላው ሰው ለመሳብ ብዙ ምክንያት እያላቸው ካለ ምክኒያት ወደ እኛ ከተሳቡ የእግዚአብሄር ሞገስ በስራ ላይ ነው ማለት ነው፡፡
ከመከራውም ሁሉ አወጣው፥ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፥ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው። የሐዋርያት ሥራ 7፡10
4.     ሰዎች ስህተታችንን በቀላሉ ካለፉት የእግዚአብሄር ሞገስ ከእኛ ጋር ነው
ሰዎች አጥፍተንም የማይጨክኑብን ከሆነ የእግዚአብሄርን የሞገስ ስራን በህይወታችን አናስተውላለን፡፡ በሰዎች ፊት ሞገስ ካገኘን ሰዎች የስህተት ንግግራችንን አስተካልው ይሰሙታል፡፡ በሰዎች ፊት ሞገስ ስናገኝ ሰዎች በተለምዶ የማይቀበሉትን የሚያበሳጫቸውን ኑሮዋችንን አስተካክለው ያነቡታል፡፡ ሰዎች ስህተታችን የሚያንስባቸው ብርታታችን የሚያይልባቸው ከሆነ በፊታቸው ሞገስን አግኝተናል፡፡ 
ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፥ በዓይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ የመንግሥቱንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ፥ በአስጢንም ፋንታ አነገሣት። መጽሐፈ አስቴር 2፡17
5.     ሰዎች ምንም ይሁን ከእኛ ወገን ከቆሙ የእግዚአብሄር ሞገስ አንደኛው ማረጋገጫ ነው
ሰዎች ስህተታችን ለማጋለጥ ሳይሆን ለመሸፈን ከተጉ በፊታቸው ሞገስ አግኝተናል ማለት ነው፡፡ ሰዎች የእኛ ጉድለት እንደራሳቸው ጉድለት ለመቁጠር ከእኛ ጋር ራሳቸውን ካስተባበሩ እግዚአብሄር በፊታቸው ሞገስን ሰጥቶናል ማለት ነው፡፡ 
አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤ መዝሙረ ዳዊት 106፡4
6.     ጠላት መሆን የሚገባቸው ሰዎች ከእኛ ጋር ሰላም ከሆኑ የእግዚአብሄር ሞገስ ከእኛ ጋር እየሰራ እንደሆነ ያመልክታል፡፡ የሚጠሉን ሰዎች በእኛ ላይ ክፋት እንዳያደርጉ የሚያደርጋቸው እና ሰላምን የሚያደርገው እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያደረገው ሞገስ ነው፡፡
የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል። መጽሐፈ ምሳሌ 16፡7
7.     ሰዎች ልመናችንን ሰምተው ካላጉላሉንና ጉዳያችንን በትጋት ከፈፀሙልን የእግዚአብሄር ሞገስ መገለጫው ነው፡፡
እግዚአብሔርም በግብፃውያን ፊት ለሕዝቡ ሞገስን ሰጠው። ሙሴም በፈርዖን ባሪያዎችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ አገር እጅግ የከበረ ሰው ነበረ። ኦሪት ዘጸአት 11፡3
የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ።  ኦሪት ዘጸአት 12፡35-36
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ሞገስ #ተቀባይነት #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መጠበቅ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መፈለግ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መታዘዝ #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment