Popular Posts

Wednesday, October 2, 2019

የፍቅር አውራ ጎዳና




ፍቅር ከሁሉም የሚበልጥ መንገድ ነው፡፡ ፍቅር ከስጦታዎች ሁሉ ይበልጣል፡፡ ፍቅር ከሃብት እና ንብረት ሁሉ ይበልጣል፡፡
ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡31
በመኪና ስትሄዱ ትንንሽ መንገድን ላየ በነዳችሁ መጠን የምትፈልጉበት ቦታ በቀላሉ ለመድረስ ጭንቅ ነው፡፡ ትንንሽ መንገድን ላይ መኪናን ለመንዳት በሞከራችሁ መጠን ግርግሩ ይበዛል፡፡ ትንንሽ መንገድ በተጠቀማችሁ መጠን መዘግየትና መቆም የተለመደ እና ግዴታ ነው፡፡
ላለመዘግየት ለመፍጠንና በራሳችሁ ፍጥነት ለመሄድ ከተፈለገ እንደ አውራ ጎዳና ያለ መንገድ ምቹ መንገድ የለም፡፡
አውራ ጎዳና ልዩ ነፃነት ይሰጣችኋል፡፡ አውራ ጎዳና ከፍ ብላችሁ በከፍተኛ ፍጥነት እንድትነዱ ያስችላችኋል፡፡
እንዲሁም ፍቅር ከሁኔታዎች ሁሉ በላይ ከፍ ብለን እንድንሄድ ያስችለናል፡፡ በፍቅር መንገድ ይቅር አለማለት ከመንገዳችን አያዘገየንም፡፡ በፍቅር መንገድ ከሁኔታዎች ሁሉ ከፍ ብለን ስለምንበር በመንገዱ መራርነት የለም፡፡ በፍቅር መንገድ እግዚአብሄር እንደፈጠረን ለመኖር ነፃነት እናገኛለን፡፡
በፍቅር መንገድ በነፃነት ለሌሎች መልካምን ለማሰብ እንችላለን፡፡ በፍቅር መንገድ ለሌሎች መልካምን መናገር ማንም አይከልክለንም፡፡ በፍቅር አውራ ጎዳና ለሌሎች መልካምን ለማድረግ የሚከለክለን ህግ የለም፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡22-23
ፍቅር ከህግ ሁሉ በላይ ስለሆነ በፍቅር የሚኖር ሰው ህግን እጥሳለሁ ብሎ የሚጨነቅበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሰው የፍቅር ህግን ብቻ በመከተል ስለሌላ ሳያስብ እግዚአብሄርን ብቻ ማስደሰት ይችላል፡፡ ሌሎች ህጎች የተሰጡት የፍቅር ህግ ምን እንደሆነ እንዲተነትኑና እንዲተረጉሙ ብቻ ነው እንጂ እግዚአብሄር ከፍቅር ህግ ውጭ ሌላ ምንም ህግ የለውም፡፡
ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል። የማቴዎስ ወንጌል 22፡38-40
አውሮፕላን ለምድር የመንገድ ህግ እንደማይገዛ ሁሉ ፍቅር ከህግ ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ የሚበር ህጎች ሁሉ ለእርሱ የሚገዙለት እርሱ ለማንም የማይገዛ ከፍ ያለ ህግ ነው፡፡
እያንዳንዱ ድርጊታችን በፍቅር እንደተደረገና እንዳልተደረገ በእግዚአብሄር ይፈተናል፡፡ በፍቅር ያልተደረገ ማንኛውም ሃይማኖታዊ ድርጊትም ቢሆን ኪሳራ ነው፡፡ በፍቅር ያልተደረገ ማንኛውም ታላቅ ነገር በእግዚአብሄር እይታ ከንቱ ነው፡፡  
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡1-3
ከሁሉ የሚበልጠውን የፍቅር መንገድን ከያዛችሁ ከአላማችሁና ከግባችሁ የሚያዘገያችሁና የሚያስቆማችሁ ማንም ነገር አይኖርም፡፡
ስለሰው ለምን መልካም አሰብክ ብሎ የሚቀጣ ህግ የለም፡፡ ስለሰው ለምንም መልካም ተናገርክ ብሎ የሚቆጣ አምላክ የለም፡፡ ለሰው ለምን መልካም አደረግክ ብሎ የሚከስ ሰው የለም፡፡ ከሌላው ሰው መልስን ሳይጠብቅ መልካምን የሚያስብ የሚናገርና የሚያደርግ ሰው ከህይወት አላማ የሚያግደው ምንም ነገር የለም፡፡
ፍቅር ራሱ የህግ ፍፃሜ ነው፡፡ የትኛውም ህግ የሚለካው በፍቅር ህግ ነው፡፡ የትኛውም ህግ ከፍቅር ህግ ጋር ካልሄደ አይፀናም፡፡ ትእዛዛት ሁሉ የፍቅር ህግ ትንተናዎች ናቸው፡፡ የትእዛዛት አላማ ሰው ከእግዚአብሄርና ከሌላው ሰው ጋር በፍቅር እንዲኖር መርዳት ነው፡፡
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡5
ፍቅር ምንም አይወጣለትም፡፡ ፍቅር ንፁህ ነው፡፡ የማንኛውም ትእዛዝ ንፅህና የሚለካው በፍቅር ህግ ነው፡፡ ፍቅር ወንድሙን አይበድልም፡፡ ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም፡፡ በፍቅር የሚኖር ሰው ህግን ሁሉ ፈፅሞታል፡፡
እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡8-10
ፍቅር ከፍ ያለ ላይኛው ሰማያዊ ጥበብ ነው፡፡
ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የያዕቆብ መልእክት 3፡17
ቅርንጫፍ በግንዱ ላይ እንደሚንጠለጠል የትኛውም ህግ በፍቅር ህግ ላይ ይንጠለጠላል፡፡ ፍቅር የትእዛዛቶች ሁሉ መሰረት ነው፡፡ ፍቅር የትእዛዛት ሁሉ ፊተኛ ነው፡፡
እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡13
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ቃል #መሰረት #ትእዛዝ #መስጠት #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment