Popular Posts

Thursday, October 10, 2019

የግንኙነት ስምረት



ሰው ብቻውን ብዙ ነገር ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሰው በግሉ በብዙ ነገሮች የተወሰነ ነው፡፡ ሰው እጅግ ታላላቅ ነገሮችን ሊያደርግ የሚችልበት እምቅ ጉልበቱ የሚለቀቀው በግንኙነት ውስጥ ነው፡፡  
ሰው ብቻውን ሊፈፅም ከሚችለው ነገር ሁሉ ይልቅ በግንኙነት ሊፈፀም የሚችለው ነገር እጅግ ይበልጣል፡፡ ለስኬትና ለፍሬያማነት ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡ ለእድገትና ለመስፋት ግንኙነት ግድ ይላል፡፡
ግንኙነት የራሱ ህግ አለው፡፡ ግንኙነት የራሱ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ በህጉ ከተመላለስን ግንኙነት ይባርከናል፡፡ በህጉ ካልተመላለስን ግንኙነት የሚገባውን ያክል ሊጠቅመን አይችልም፡፡ ከግንኙነት የተሻለ ነገር ማውጣት የምንችለው የግንኙነትን መሰረታዊ ህጎች ስንረዳ ነው፡፡
ማንኛውም ውድድር ህግ አለው፡፡ ህግ የሌለው ውድድር የለም፡፡ ውድድርን ውድድር የሚያደርገው ህጉን ጠብቆ መወዳደር ነው፡፡
ከሰው ልጅ ግንኙነቶች እጅግ በጣም ወሳኙ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ የሰው ህይወት ስኬት ከእግዚአብሄር ጋር ባለው ግንኙነት ይወሰናል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ጥበብ የጥበብ ሁሉ መሰረታዊ ጥበብ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተውረው ስለዚህ ነው ፡፡ ሰው የብዙ ግንኙነቶች አዋቂ ቢሆን ከእግዚአብሄር ጋር ባለው ግንኙነት አላዋቂ ከሆነ ከንቱ ነው፡፡ በሌሎች ግንኙነቶች ሁሉ ከተካነና ከእግዚአብሄር ጋር ባለ ግንኙነት ጥበብ ከጎደለው ሰው በላይ ምስኪን ሰው የለም፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 1፡7
ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት እንደሚገባ ከያዝን ሌሎች ግንኙነቶች ሁሉ ትክክለኛ ስፍራቸውን ይይዛሉ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ይህ ወሳኝ ግንኙነት ከተበላሸ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ጋር ያለን ግንኙነት ይበላሻል፡፡ ሰው በህይወቱ የሚገጥመው ማንኛውም ውድቀት ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት መበላሸት ውጤት ነው፡፡
እግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት የራሱ መሰረታዊ ህጎች አሉት፡፡ እግዚአብሄር ከሰው በጣም ብዙ ነገሮችን አይጠብቅም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን አያስጨንቅም፡፡
ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። 1 የዮሐንስ መልእክት 5፡3
እግዚአብሄር ሰውን ከሚችለው በላይ እንዲፈተን አይፈቅድምን፡፡
እግዚአብሄ በአንድ ቀን ራሱን ሰጥቶ ይጨርሳል ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ምን እንዳደረግነውና ምን ያህል ታማኝ እንደሆንን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ግንኙነት እግዚአብሄር ራሱን ይበልጥ የሚሰጠን እነዚህ የግንኙነት ህጎች ስንረዳ ብቻ ነው፡፡ እነዚህን መፅሃፍ ቅዱሳዊ የግንኙነት ህጎች በተረዳንና በእለት ተእለት ኑሮዋችን በተገበርናቸው መጠን ከቀን ወደቀን እግዚአብሄር ራሱን ይበልጥ እየሰጠን ይሄዳል፡፡
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የዮሐንስ ወንጌል 14፡23
በእግዚአብሄር እና በሰው መካካል ያለው ግንኙነት እንዲሰምር እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው መሰረታዊ ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሚጠይቀውን ሰውም ሊያደርግ የሚችለውን ነገሮች ከመፅሃፍ ቅዱስ እንመልከት፡፡
1.      ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነቱ የሚሰምረው ሰው ከእግዚአብሄር ጋር በትህትና ሲኖር ነው፡፡
እግዚአብሄር ፈጣሪያችን አምላካችንም ነው እንጂ የቆሎ ጓደኛችን እኩያችን አይደለም፡፡ ካለትህትና ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ይሰምራል ማለት ዘበት ነው፡፡
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ትንቢተ ሚክያስ 6፡8
2.     ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ባለው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ የሚሆነው እግዚአብሄርን ሲያመሰግን ነው፡፡
እግዚአብሄር በጥበብ እና በሃይል ታላቅ ነው፡፡ ይህን በጥበብና በሃይል ታላቅ የሆነን አምላክ ለታላቅነቱ እውቅና ከመንፈግ  የበለጠ ግንኙነቱን የሚያበላሽ ነገር የለም፡፡ ስናጉረመርም የእግዚአብሄርን ቻይነት ጥያቄ ውስጥ እናስገባለን፡፡ ስናጉረመርም ከእግዚአብሄር በላይ እንዳወቅን እናስመስላን፡፡ ስናንጐርጕር ከእግዚአብሄር በላይ ጥበብኛ እንደሆንን እንመካለን፡፡
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡10
ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።  1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡17-18
3.     ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት የሚሰምረው ሰው የእግዚአብሄርን እርምጃ ሲታገስ ነው፡፡
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄርን እኛ አናጣድፈውም፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ፕሮግራም ውስጥ አይገባም፡፡ እግዚአብሄር  ለእኛ ሙሉ ፕሮግራም አለው፡፡ እግዚአብሄር ራሱ እርምጃ ፍጥነት አለው፡፡ የእግዚአብሄርን የእርምጃ ፍጥነት መረዳትና መታገስ ግንኙነታቸን እንዲዳብር እና ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋል፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። መጽሐፈ ምሳሌ 13፡11
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። መጽሐፈ ምሳሌ 28፡20
4.     ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት የሚበለፅገው ሰው ከእግዚአብሄር በላይ የሚወደው ነገር ከሌለ ብቻ ነው፡፡
እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። የሉቃስ ወንጌል 10፡27
እግዚአብሄር ታላቅ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፍቅር አምላክ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር በሰላም መኖር ከፈለገ እግዚአብሄርን በሚያንስ ነገር ማስቀናት የለበትም፡፡  
የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 1፡23
እግዚአብሄርን ታላቅ አምላክ ስለሆነ ብናስቀናው የምንጎዳው እነኛ እንጂ አርሱ አይደለም፡፡
ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡22
5.     ከእግዚአብሄር ጋር ያለው የሰውን ግንኙነት ከሚያሳኩ ነገሮች አንዱ እግዚአብሄርን መፈለግ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ያወቀ ሰው እግዚአብሄርን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር መልካም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ይፈለጋል፡፡ ምንም ነገር ከመፈለግ ይበልጥ እግዚአብሄርን መፈለግ ዋጋ እንደሚያሰጥ ማወቅ ጥበብ ነው፡፡
ስወ ምንም ነገር በመፈለግ ቢሳሳት እግዚአብሄርን አብዝቶ በመለጉ አይሳሳትም፡፡ ሳው በምንም መፈለግ ቢከስር እግዚአብሄ በመፈለግ ያተርፋል እንጂ አይከስርም፡፡ እግዚአብሄር እንደ መፈለግ አስተማማኝ ኢንቨስትመንት የለም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
እግዚአብሄርን መልካምነት በተረዳን መጠን አብዘተን እንድንፈልገው ያደርጋናል፡፡ ሰው እያደገ ሲሄድ እግዚአብሄርን የሚፈልግበት መንገዱ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ሰው እየበሰለ መሄዱ የሚታወቀው በሁሉ ነገር እግዚአብሄርን መፈለግ ሲጀምር ነው፡፡ እግዚአብሄርን የምንፈልገው ለእግዚአብሄር ጥቅም ሳይሆን ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ በዋነኝነት የሚጠቅመው እኛን ነው፡፡  
6.     ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት የሚሰምረው እግዚአብሄርን ሲጠብቅ ነው፡፡
እግዚአብሄር ይወደናል፡፡ እግዚአብሄር እኛን ይፈልገናል፡፡ እግዚአብሄር እኛን ይናፍቀናል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ስንቆይ ከእግዚአብሄር የሚገኘውን የፀሎት መልሳችንን ሳይሆን እግዚአብሄርን ራሱን ስንደሰትበት ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ይዳብራል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን እንደ አባት ካላናገርነው ከእርሱ ጋር ዝም ብለን ጊዜ ማሳለፍ ካልፈለግን ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ይዳብራል ብሎም ፍሬያማ ይሆናል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡
ወደ እግዚአብሄር ስንቀርብ ለመስማት እንጂ ተናግሮ ለመሄድ መሆን የለበትም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት የሚሰምረው ስንናገርና ስንሰማ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ለመስማት ደግሞ በእግዚአብሄር ፊት መቆየት ይጠይቃል፡፡ ለእግዚአብሄር ከመናገራችን በፊት እግዚአብሄርን መስማት ይጠይቃል፡፡
አንዳንዴ ካለምንም የፀሎት ርእስ በእግዚአብሄር ፊት በመቆየት ልናመሰግነውና ልናደንቀውና ይገባናል፡፡
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። የሐዋርያት ሥራ 13፡2
7.     ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት የሚሰምረው እግዚአብሄርን ሲታዘዝ ነው፡፡
የተፈጠረነው እግዚአብሄርን ለመታዘዝ ስለሆነ እግዚአብሄርን ስንታዘዝ ነፃ እንሆናለን፡፡ እግዚአብሄርን የምናገኘው በቃሉ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት የሚወሰነው በቃሉ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያላም፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ ውስጥ ለሚፈልገው ሰው ሁሉ ራሱን ሰጥቶዋል፡፡ ከቃሉ ውጭ እግዚአብሄር የምናገኝበት ሌላ አስማታዊ ስራ የለም፡፡  
ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። የዮሐንስ ወንጌል 8፡31-32
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 11፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ግንኙነት #ትህትና #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መጠበቅ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መፈለግ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መታዘዝ #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment