“አንድ ሰው ማርጀቱን የሚያውቀው በተስፋ መኖሩን
ትቶ በትዝታ መኖር ሲጀምር ነው” የሚባል የተለመደ አባባል አለ፡፡
እውነተኛ አባባል ነው፡፡ ሰው ለመውጣትና ለመውረስ
ሙሉ ጉልበትን ይዞ ልቡ ግን ካረጃ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡
ኢያሱ ሊወርሰው የሚችለው ብዙ ምድር ቢኖርም ኢያሱ
ግን ስላረጀ መውረስ እንደማይችል እግዚአብሄር ስለኢያሱ ሲመሰከር እንመለከታለን፡፡
ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ እግዚአብሔርም አለው፦ አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤ መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 13፡1
ሰው እድሜው እየጨመረ ሲሄድ በጥበብና በማስተዋል
እያደገ ይሄዳል፡፡ ሰው በእድሜ እየጨመረ ሲሄድ በህይወት የሚሰራበትንና የማይሰራበትን መንገድ በልምድ ማወቅና መረዳት ይጀምራል፡፡
ሰው በእድሜ እየጨመረ ሲሄድ ጥፋት እየቀነሰ ልማት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ሰው በእድሜ ጥበብን በጨመረ መጠን ብክነት እየቀነሰ ውጤታማነትን
እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው። ወደ ዕብራውያን 5፡14
ሰው
የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ህይወቱ ዋናው ፈተናው የእግዚአብሄርን አሰራር መረዳት ነው፡፡
ሰው
በጌታ ቤት በእድሜ እየጨመረ ሲሄድ ክፉውንና መልካሙን ለመለየት ሰፊ ልምድን ያካብታል፡፡ ሰው በጌታ ቃል እየኖረ ሲሄድ እግዚአብሄርን
ይበልጥ እያወቀ ከብዙ እስራቶች ነፃ እየወጣ ይሄዳል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄርን ጋር በኖረ መጠን እግዚአብሄር የሚሰራበትንና የማይሰራበትን
መንገድ በቀላሉ ስለሚረዳ ጌታን በቅርብ ለመከተል ይቀለዋል፡፡
ኢየሱስም
ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።
የዮሐንስ ወንጌል 8፡31-32
ሰው
ከእግዚአብሄር ጋር ኖሮ ጌታ ኢየሱስን ተከትሎ የእግዚአብሄርን አሰራር መረዳት ሲጀምር ፈተናው የልብ እርጅና ፈተና ይሆናል፡፡ የእርጅና
ፈተና የሚመጣው የእግዚአብሄር ቃል እንዴት እንደሚሰራ መረዳት ስንጀምር ነው፡፡
ስለእርጅና
ስናወራ የምናወራው ስለእድሜ መጨመር አይደለም፡፡ የእድሜ መጨመረ ማንም ሊያመልጥበት የማይችል በምድር ላይ የሚኖር ሰው ሁሉ እጣ ፈንታ ነው፡፡ እንዲያውም የሰው እድሜ መጨመር እግዚአብሄር እንደታገሰው
የክብር ምልክት ነው፡፡
የሸበተ
ጠጕር የክብር ዘውድ ነው፥ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል። መጽሐፈ ምሳሌ 16፡31
እድሜያችን
ሲጨምር ታዲያ የመውጣትና የመውረስ ፍላጎታችን እየጨመረ እንጂ በፍፁም እየቀነሰ መሄድ የለበትም፡፡
ስለእርጅና
ስናወራ የምናወራው ከጊዜው በፊት ዋጋን የመክፈልና የመውረስ ፍላጎት ማጣትን እያወራን ነው፡፡ ስለእርጅና ስናወራ የምናወራው በመውረሻ
ጊዜያችን ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆንንና የልብን መቀዝቀዝን ነው፡፡ ስለእርጅና ስናወራ የምናወራው ከጊዜው በፊት የልብን ፍላጎት
ማጣትን ነው፡፡ ስለእርጅና ስናወራ የምናወራው ከጊዜው በፊት የልብን እሳት ማጣት እና አላግባብ ዋጋ ለመክፈል መሳሳትን ነው፡፡
ሰው
እንዳይወጣ እንዳይወርስ በእድሜ ከመጨመሩ በላይ የሚፈታተነው የልብ እርጅና ነው፡፡ ሰው በመጀመሪያዎቹ ጌታን በተከተለባቸው አመታት
ደስ ብሎት ለጌታ ዋጋን ይከፍላል፡፡ ሰው እየቆየ ሲሄድ ግን ለእግዚአብሄር ነገር ዋጋ ላለመክፈል ይፈተናል፡፡ ሰው እየቆየ ሲሄድ
ሰው ከመጠን በላይ ለራሱ እየሳሳ ይሄዳል፡፡ ሰው እየቆየ ሲሄድ ራሱን አደጋ ላይ ላለመጣል "ሪስክ" ላለመውሰድ
ይሳሳል፡፡ ሰው እየቆየ ሲሄድ በህይወቱ ከገጠመው ውድቀት አንፃር አዲስ ነገርን ለመሞከር ይበልጥ እይፈራ ይሄዳል፡፡ ሰው እየቆየ
ሲሄድ ላለመጎዳት ከመጠን በላይ መጠንቀቅ ይጀምራል፡፡ ሰው እየቆየ ሲሄድ የምቾት ቀጠናውን ለመተው እምቢተኛ ይሆናል፡፡
በክርስትና
ህይወትና አገልግሎት ደግሞ ስኬታማ የሚኮነው በእምነት ብቻ ነው፡፡ እምነት ደግሞ እግዚአብሄር ያለውን ሰምቶ ተጋላጭ የመሆን ወይም
ሪስክ የመውሰድ ጉዳይ ነው፡፡
ሰው
እግዚአብሄር ለመራው ነገር ዋጋ መክፈል ካቃተው በልብ እርጅና ተይዟል ማለት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ለመራው ነገር የሚከፍለው
ዋጋ ከሚያገኘው ጥቅም ከበለጠበት በልብ እርጅና በሽታ እየተቃየ ነው ማለት ነው፡፡
እግዚአብሄር
የእስራኤልን ህዝብ የገባላቸውን የተስፋ ምድር ተዋግቶ እንዲያስወርስ ለመላክ አልቻለም ነበር፡፡ ኢያሱን በእርጅና ምክኒያት ያልተወረሱትን ምድሮች ለመውረስ በእግዚአብሄር መላክ
አይችልም ነበር፡፡
ሰው
ልቡ ሲያረጅ መውጣት መግባት መውረስ እየቻለ ልቡ ድክም ይላል፡፡ ሰው ልቡ ሲያረጅ መውጣት መግባት መውረስ እየቻለ እግሩን ዘርግቶ
እንዳይራመድ ስንፍና ይጫጫነዋል፡፡ ሰው ልብ ሲያረጅ የሚያወጣውን ወጭ በጣም ከማጋነኑ የተነሳ የሚያገኘውን እግዚአብሄርን በመታዘዝ
የሚያገኘውን ዘላለማዊ ትርፍ አያስበውም፡፡ ሰው ልቡ ሲያረጅ ያለውን መጠበቅ እንጂ ሌላ መጨመር አያስብም፡፡ ሰው ለመውጣት ለመውረስ
ያለው እድል በህይወት እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ሰው ወደሚሄድበት እነዚህ ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይኖሩም፡፡
አንተ
በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። መጽሐፈ መክብብ
9፡10
ከእግዚአብሄር
ጋር በኖርን መጠን የመውጣትና የመውረስ ፍላጎታችን በዚያው መጠን መጨመር እንጂ መቀነስ የለበትም፡፡ በጌታ ያለን ልምምድ እየጨመረ
ሲሄድ የመውጣት የመውረስ እምነታችን ካልጨመረ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በጌታ ቤት በቆየን መጠን ጌታን ለመታዘዝ ለመውረስ እየሰነፉ
መሄድ የመንፈሳዊ ጤንነት ምልክት አይደለም፡፡ ትክክለኛው እድገት በእድሜያችን መጠን ልባችን ሲታደስ ፍሬያችንም ሲበዛ ነው፡፡
ጻድቅ
እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ፤ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ። መዝሙረ ዳዊት 92፡12-14
የህይወት
ፈተና አላማው እምነታችንን እንዲያጠራና እንዲያከብረው እንጂ እንዲያጠፋው አይደለም፡፡
በዚህም
እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ
ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡6-7
ካሌብ
እድሜው በጨመረ ቁጥር ሃይሉን እንደዚያው ይጨምር ነበር፡፡
አሁንም፥
እነሆ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፥ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፥ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን
አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ፥
ዛሬ ጕልበታም ነኝ፤ ጕልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ዛሬ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው። መጽሐፈ
ኢያሱ ወልደ ነዌ 14፡10-11
የክርስትያን
ህይወት ሙሉ ቀን እስከሚሆን ካለማቋረጥ እየጨመረ እንደሚበራ የንጋት ፀሃይ እንጂ እንደሚጠልቅ የምሽት ጀንበር አይደለም፡፡
ጫማህ
ብረትና ናስ ይሆናል፤ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል። ኦሪት ዘዳግም 33፡25
እግዚአብሄርን
የሚጠብቅ ሰው ሃይሉ እየታደሰ አስከመጨረሻው በብቃት ይጨርሳል እንጂ ከመንገድ አይመለስም፡፡
ምኞትሽን
ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል። መዝሙረ ዳዊት 103፡5
ለተጨማሪ
ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ
መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ
#ጌታ #እሳት #ህብረት #ቃል #ሽበት #ሽምግልና #ድፍረት #መቀጣጠል #ክብር #አገልግሎት #መዋረድ #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment