Popular Posts

Saturday, October 12, 2019

የእግዚአብሔር ሰው ሆይ



አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡11
እግዚአብሄርን በተለይ በአምስቱ የአገልግሎት ስጦታዎች የሚያገለግሉት ሐዋርያት ፥ ነቢያት፥ ወንጌልን ሰባኪዎች፥ እረኞችና አስተማሪዎች የእግዚአብሄር ሰው ተብለው ሲጠሩ እንሰማለን፡፡ እውነት ነው በእነዚህ የአገልግሎት ስጦታዎች የሚያገለግሉ ሁሉ የእግዚአብሄር ሰው መሆን ይገባቸዋል፡፡
ነገር ግን የእግዚአብሄር ሰው የሚለው አገላለፅ ለእግዚአብሄር ለሚኖር ሰው ሁሉ የሚሰጥ መጠሪያ ስም እንጂ ለጥቂት አገልጋዮች የሚሰጥ የማእረግ ስም አይደለም፡፡
እነዚህን እግዚአብሄርን የመምሰል ባህሪያትን በህይወቱ የሚያሳይ ማንኛውም ሰው የእግዚአብሄር ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ማለት ለእግዚአብሄር እንጂ ለሌላ ነገር የማይኖር ለእግዚአብሄር የተሰጠ ሰው ማለት ነው፡፡
አገልጋይ ነኝ ቢልም እንኳን እነዚህን እግዚአብሄርን የመምሰል ባህሪያት የማያሳይ ማንኛውም ሰው ግን የእግዚአብሄር ሰው ሊባል አይገባውም፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ባህሪ የሚያሳየውን ሰው ሰዎች እንደ ማእረግ ሳይሆን እንደ መግለጫ የእግዚአብሄር ሰው ብለው ይጠሩታል፡፡ ሰዎች የክርስትያኑን ህይወቱን ተመልከተው የእግዚአብሄር ሰው ይበሉት እንጂ የእግዚአብሄር ሰው ካላሉት መቆጣትና መናደድ የለበትም፡፡ ሰው ራሱን የእግዚአብሄር ሰው የሚል ማእረግ ሰጥቶ የእግዚአብሄር ሰው በሉኝ ማለት የለበትም፡፡
የእግዚአብሄር ሰው የሚያስብሉትን ባህሪያት ከመፅሃፍ ቅዱስ እንመልከት
1.      ገንዘብን ከመውደድ የሚሸሽ ሰው
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡10-11
ገንዘብን የሚወድ ሰው የገንዘብ ሰው እንጂ የእግዚአብሄር ሰው አይባልም፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ባለው የሚረካ ያለኝ ይበቃኛል የሚል ራሱን የሚያማጥን ሰው ነው፡፡  
አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡3-5
2.     ጽድቅን የሚከታተል  
የእግዚአብሄር ሰው የፅድቅ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በእግዚአብሄር ዘንድ ትክክል መሆኑን ራሱን ሁልጊዜ የሚፈትሽ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው እንደ እግዚአብሄር ቃል ትክክለኛውን ነገር ማድረጉን በማረጋገጥ በማስተዋል የሚራመድ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው የማይገባውን የማያደርግ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በላይኛይቱ ጥበብ በመራመድ ፅድቅን በትጋት የሚዘራ ሰው ነው፡፡
ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል። የያዕቆብ መልእክት 3፡17-18
3.     እግዚአብሔርን መምሰል
የእግዚአብሄር ሰው በህይወቱ ክርስቶስን የሚመስል ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው የክርስቶስ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው የክርስቶስን ባህሪ በህይወቱ የሚያሳይ ሌሎችን የሚያስቀድም ራስ ወዳድ ያልሆነ ትሁት ሰው ነው፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡5፣7-8
4.     እምነትን የሚኖር
የእግዚአብሄር ሰው የእምነት ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ሁልጊዜ በማይመስል ሁኔታ ውስጥ እንኳን እግዚአብሄርን በማመኑ ይታወቃል፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በሰዎች ላይ አይታመንም፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በሁኔታ ላይ አይደገፍም፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በእግዚአብሄር ቃል ላይ የሚቆም ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ላይ የሚቆም ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው የሚመላለሰው በተፈጥሮ አይን በሚታየው ሳይሆን በተፈጥሮ አይን በማይታየው ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ . . . የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡17-18
5.     ፍቅር
የእግዚአብሄር ሰው እግዚአብሄርንና ሰውን የሚወድ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ለእግዚአብሄርና ለሰው መልካም የሚያስብ መልካም የሚናገርና መልካም የሚያደርግ ፍቅር ያለው ሰው ነው፡፡
አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። የማርቆስ ወንጌል 12፡30-31
6.     መጽናትን ይከታተላል
የእግዚአብሄር ሰው በፅናቱ ይታወቃል፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ወረተኛ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ሰው የእግዚአብሄር ፈቃድ ካደረገ በኋላ ይታገሳል፡፡ የእግዚአብሄር ሰው እግዚአብሄርንና ሰውን ይታገሳል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይጠብቃል፡፡ የእግዚአብሄር ሰው በታማኝነቱ እና በመፅናቱ ይታወቃል፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ወደ ዕብራውያን 10፡36
7.     የዋህነት
የእግዚአብሄር ሰው በየዋህነቱ ይታወቃል፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ያለውን ተፅእኖውን ለክፋት ባለመጠቀም ይታወቃል፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ክፉ ለማድርግ ሃይሉና እድሉን እግኝቶ ክፉ ላለማድረግ የወሰነ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰው ክፉ ለሚያደርግበት ሰው መልካም በማድረግ ይታወቃል፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡22
አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #እምነት #ህይወት #የገንዘብፍቅር #የዋህነት #መጽናት #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እግዚአብሔርንመምሰል #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

No comments:

Post a Comment