Popular Posts

Tuesday, October 15, 2019

በትናንት እና በነገ መካከል የመኖር ወርቃማ እድል ክፍል 1



ትናንት ታሪክ ነገ ደግሞ ተስፋ ነው፡፡ አሁን ያለን ዛሬ ብቻ ነው፡፡
ምንም ያህል ብንመኝ ትላንትን መለወጥ አንችልም፡፡ ምንም ያህል ብንተጋ ትላንትን ማስተካከለ እንችልም፡፡
ምንም ያህል ብንፀፀት ትላንትን አንመለስም፡፡ ፀፀት ሞት እንጂ ሌላ ምንም አያመጣም፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 710
ስለትላንት መፀፀት ትላንት አያስተካክልም ዛሬን ግን ያበላሻል፡፡ የትላንት ፀፀት የዛሬን ንፅህና ይበርዛል፡፡ የትላንት ፀፀት የዛሬን እንደ አዲስ የመጀመር እድል ያበላሻል፡፡
እግዚአብሄር ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በየእለቱ አዲስን እድል ወደ ህይወታችን ያመጣል፡፡
እግዚአብሄር ዘመናችንን በቀን የከፋፈለው የትላንቱን ትተን በዛሬ ላይ እንድንኖር ትላንትንና ዛሬን እየለያቸው ነው፡፡ እግዚአብሄር ትላንትንና ዛሬን ያልደባለቀው አዲስን እድል እየሰጠንነው፡፡
ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡22-23
ትላንትን ካልተውን ወደዛሬ ካመጣነው ዛሬን እናበላሸዋለን፡፡
ጆይስ ማይር ስትናገር የትላንትን መልካምነት እያሰበ ዛሬ ላይ የሚኖር ሰው ሳያውቀው ትላንትን አሮጌውን ቀን ዛሬ ደግሞ ይኖረዋል፡፡ ዛሬን እስከሚንቅ ድረስ በትላንት በጣም የተማረከ ሰው ከዛሬ ትላንት ይሻላል እያለ ነው በማለት ታስተምራለች፡፡
በትላንት  ላይ የቆመ ሰው ሳያውቅ ትላንትን ደግሞ ደጋግሞ በዛሬ ላይ ይኖረዋል፡፡ ዛሬ ምንም አዲስ ቢሆንም ትላንትን በዛሬ ላይ እየኖረ አዲሱን ትላንትን ያበላሸዋል፡፡  
ትላንት በህይወታችን ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ዛሬም በህይወታችን የራሱ ስፍራ አለው፡፡ ትላንት ታሪክ ነው፡፡ በትላንት እንማራለን፡፡ ትላንት እስከ ክብሩና  ድካሙ ያለፈ ቀን ትላንት ነው፡፡ ትላንትን ደግመን አንኖረውም፡፡ ትላንት ከዛሬ አይሻልም፡፡   
ትላንት ምንም መልካም ቢሆን ዛሬን ሊተካ አይችልም፡፡ የዛሬ ጎዶሎ የትላንትን ሙላት ይበልጣል፡፡ የዛሬ ውርደት የትላንትን ክብር ይበልጣል፡፡ የዛሬ ድካም የትላንትን ብርታት ይበልጣል፡፡ ከትላንት አንበሳ የዛሬ ውሻ ይበልጣል፡፡
ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። መጽሐፈ መክብብ 9፡4
ዛሬ ላይ ቆሞ በትላንት ላይ መኖር ሞኝነት እንጂ ጥበብ አይደለም፡፡
ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና። መጽሐፈ መክብብ 7፡10
ትላንት ምንም ብንመኝ ያላገኘነውን ዛሬ ያገኘነው አሁን ብቻ ነው፡፡ ትላንት ላይ ቆመን ተራራ የሆነብን ነገ የተደረሰበትና የተገኘው ዛሬ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የምንኖረው ኑሮ የትላንት ህልማችን ነው፡፡  
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #ውብ #አሁን #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ

No comments:

Post a Comment