Popular Posts

Friday, October 11, 2019

ከ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ የዶክተር አቢይ አህመድ የታዘብኩት



በተለያየ መልኩ ከተማርኩት የመሪነት መርሆዎች አንፃር ፣ እኔም በህይወቴ ካለፍኩባቸው የተለያዩ መሪነት ሃላፊነቶች አንፃር ከዶክተር አቢይ የመሪነት ባህሪያት የታዘብኩትን ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡  
መሪነት የተፅእኖ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፌ ዶክተር አቢይ በጥቂት ወራት ውስጥ በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ ያሳደሩትን ተፅእኖ ለመዘርዘር ወደድኩ፡፡
1.      ፍትህ
ዶክተር አቢይ ህዝቡን ካስደመሙበት ባህሪያት አንዱ ፍትህ ነው፡፡ ፍትህ ማለት አለማዳላት ማለት ነው፡፡ ዶክተር አቢይ የኢትዮጲያን ህዝብ እኩል የሚያዩ መሪ እንደሆኑ አስመስክረዋል፡፡ ለሰው ልጅ ያላቸው ክብር ከፍተኛ ነው፡፡ ለዶክተር አቢይ ትልቁም ሰው ትንሹም ሰው አንድ ነው፡፡ ሰውን በሰውነቱ እንጂ በዘሩ በሃብቱ በእውቀቱ እና በፆታው አይለዩም፡፡ ሰውን ሲያዩ የሚታያቸው የአገር እዳ ሳይሆን የአገር ሃብት ነው፡፡ ሰው ሁሉ ሁኔታው ከተመቻቹለት ሊነሳ ሊያድግ ሊበለፅግ እንደሚችል ያምናሉ፡፡  
2.     እውነተኝነት
ዶክተር አቢይ እውነተኛ ሰው ናቸው፡፡ በአፋቸው የሚናገሩት አንድ በልባቸው ያለው ሌላ ነገር አይደለም፡፡ የተዘጋጁት የኢትዮጲያን ህዝብ ለማገልገል ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉት ለህዝቡ እኔ አውቅልሃለሁ እያሉ የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ አይደለም፡፡ እውነት እንደምታሸንፍ ያምናሉ፡፡ ሁሌ ከእውነት ጋር ለመወገን እውነትን ለመፈለግ ይተጋሉ፡፡ የመሪነት እና የተመሪነት ጉዳይ የመተማመን ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የአገር መሪ እውነተኛ ሰው እንደሆነ የሚመራው ህዝብ ሊያመነው እና ራሱን ሊሰጠው ሊተባበረው ይገባል፡፡ ዶክተር አቢይ በእውነተኝነት የህዝቡን ልብ ያስከተሉ መሪ ናቸው፡፡      
3.     ፍቅር
ዶክተር አቢይ በፍቅራቸው ይታወቃሉ፡፡ ዶክተር አቢይ ለሰውም መልካም በማሰብ ለሰው መልካም በመናገር ለሰው መልካም በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
4.     ምህረት
ዶክተር አቢይ በምህረታቸው እንደሚታወቁ አለም የመሰከረው ነው፡፡ ዶክተር አቢይ እስረኞችን በመፍታት በምህረታቸው ይታወቃሉ፡፡ ዶክተር አቢይ የሚያበሳጩዋቸው ሰዎችን ላለማሰር በትግስታቸው ይታወቃሉ፡፡ ዶክተር አቢይ አብረዋቸው ለሚሰሩ ሰዎች ርህራሄ አላቸው፡፡ ዶክተር አቢይ የሰዎችን ድካም አለፈው ማየትና በብርታታቸው ላይ ብቻ የማተኮር ዝንባሌ አላቸው፡፡  
5.     ታማኝነት
ዶክተር አቢይ ቀን ከሌሊት ለሃገሪቱ እድገት ካለእረፍት እንዲሰሩ የሚጎተገታቸው የታማኝነት ስሜት ነው፡፡ ለህዝቡ ታማኝ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ለህዝቡ ካላቸው አክብሮት የተነሳ ህዝቡ የሰጣቸውን ሃላፊነትና ማባከን አይፈልጉም፡፡ ህዝቡ ያሳያቸውን ፍቅር እና ድጋፍ ህዝቡን መልሰው ህዝቡን በማገፈልገል መክፈል ይፈልጋሉ፡፡ ዶክተር አቢይ ህዝብን ባለቸው እውቀት ሁሉ ከማገልገል ውጭ ሌላ ድብቅ አጀንዳ ያላቸውም፡፡
6.     ባለራእይነት
ዶክተር አቢይ ከብዙ ሰዎች ከፍ ያለ ነገርን ያያሉ፡፡ ዶክተር አቢይ የኢትዮጲያን እምቅ ጉልበት ያያሉ፡፡ ኢትዮጲያ በትክክል ከተመራች የት ልትደርስ እንደምትችል ያልማሉ፡፡ ብዙ ሰዎች አሁን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ አይተው ተስፋ ሲቆርጡ ዶክተር አቢይ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ሳይሆን እየሄደችበትን ያለችውን የብልፅግና ደረጃ አይተው በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ዶክተር አቢይ በብጥብጥ ውስጥ ሰላምን ያያሉ፡፡ ዶክተር አቢይ በመቀነስ ውስጥ መጨመርን ያያሉ፡፡ ዶክትር አቢይ በውድቀት ውስጥ መነሳትን ያያሉ፡፡  
7.     ብሩህነት
ዶክተር አቢይ አእምሮዋቸው ብሩህ ነው፡፡ ዶክተር አቢይ ለውጥን አይፈሩም፡፡ ዶክተር አቢይ ውድቀትን ፈርተው መውሰድ  የሚገባቸውን አስፈላጊ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይሉም፡፡ ዶክተር አቢይ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት ሲወስኑ እጅግ የተራራቁ ሊታረቁ የማይችሉ ፅንፍ አስተሳሰቦች እንዳሉ እየተረዱት ነው፡፡ ዶክተር አቢይ ለመማር የተዘጋጁ ሰው ናቸው፡፡ ዶክተር አቢይ የአገሪቱን ፣ የቀጠናውንና እና የአለምን ወቅታዊ ሁኔታ ለማንበብ አእምሮዋቸው ክፍት ነው፡፡ ዶክተር አቢይ የኢኮኖሚ መርሆዎችን ለመረዳት አእምሮዋቸው ክፍት ነው፡፡
8.     አገልጋይነት
ዶክተር አቢይ ያላቸውን መሪነት መጠቀሚያ አጋጣሚ ሳይሆን መጥቀሚያ አጋጣሚ አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ ዶክተር አቢይ ስልጣኑን የሚመለከቱት እንደ ሸክም እንጂ እንደ ጥቅም አይደለም፡፡ ዶክተር አቢይ ስልጣኑን የሚያዩት ሰውን እንደማገልገያ አጋጣሚ እንጂ በሰው እንደ መገልገያ አጋጣሚ አይደለም፡ ዶክተር አቢይ ነገር ስልጣን ባይኖራቸው በደስታ ከስልጣናቸው ወርደው ሌላ የሚያስደስታቸውን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን የማያካብዱ ህይወታቸው ቀለል ያለ ሰው ናቸው፡፡ ዶክተር አቢይ እሳቸው ብቻ የተለዩ መሪ እንደሆኑ አያስቡም፡፡ በተለያየ ጊዜ እንደሰማሁዋቸው ይህችን አገር ለመምራት እሳቸው ብቻ እንደተመረቁና እንደተለዩ ሰው አድርገው ስለራሳቸው አያስቡም፡፡ እርሳቸው ስልጣን በሚለቁበት ጊዜ ይህችን አገር እንደእርሳቸው ወይው ከእርሳቸው የተሻለ የሚመራ መሪ እንደሚነሳ ያምናሉ፡፡ እንደተመረጡ የአንድ መሪ የመምራት ዘመን እንዲወሰን ለምክር ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡት ስለዚህም ይመስለኛል፡፡   
9.     በሰዎች ማመን
ዶክተር አቢይ በሰዎች ያምናሉ፡፡ ዶክተር አቢይ ስጋት እና ፍርሃት የለባቸውም፡፡ ዶክተር አቢይ "እሺ ጌታዬ" ብቻ የሚሉትን ሰዎች በዙሪያቸው አይሰበስቡም፡፡ ዶክተር አቢይ የተለየ አመለካት ካለው ሰው ጋር ለመስራት ስጋት የለባቸውም፡፡ ዶክተር አቢይ የእኔ የፖለቲካ ድርጅት ሰውን አምናለሁ ከእኔ የፖለቲካ ድርጅት ውጭ ያለን ሰውን አላምንም የሚል አስተሳሰብ የላቸውም፡፡ የሰውን እምቅ ጉልበት ከተረዱ የተቃዋሚ ድርጅት አባልን በማስጠጋት ለአገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይሾማሉ፡፡ ዶክትር አቢይ ሰዎችን በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ አይለኩም፡፡ ዶክተር አቢይ  ከእርሳቸው የተለየ የፖለቲካ አቋም ያለው ማንም ሰው በየትኛውም የስልጣን ደረጃ በሙያው አገሪቱን ማገልገል እንደሚችል ያምናሉ፡፡
10.    ዲሞክራቲክ
አንዳንደ ሰዎች ዲሞክራሲ ብለው የሚጮኹት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ ነው፡፡ የራሳቸውን ፍላጎት እስካላሳካ ድረስ ዲሞክራሲ የሚባለውን ነገር በመስኮት አሽቀንጥረው ነው የሚጥሉት፡፡ ዶክተር አቢይ ዲሞክራሲ ሲሉ ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን በእርሳቸውም ላይ እንደሚሰራ ተቀብለዋል፡፡ ዶክተር አቢይ ዲሞክራሲ የሚሉት ለአፋቸው አይደልም ከልባቸው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ብለው በብዛት የሚጮሁት ስልጣኑ ላይ ስላይደሉ ነው፡፡ ልክ ስልጣኑ ላይ ሲሆኑ የስልጣን እና የሃይል ፈተና በአፋቸውም ባይሆን በልባቸው የምን ዲሞክራሲ የምን የህግ የበላይነት እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ይህን ሁሉ ያደረገው እግዚአብሄር ነው፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ እግዚአብሄር ትክክለኛ መሪ እንዲነሳ አብዝቶ ፀልዮዋል፡፡ ይህ የፀሎት መልስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ዶክተርአቢይ #ኖቤልሽልማት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #አቢይአህመድ #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment