አንዳንዴ የራሳችን ጉልበት ያልቃል፡፡ አቅም ያንሰናል፡፡ ማለዳ ብርቱና ሙሉ ሆነን ከሰአት በኋላ ውድቅ እንላለን፡፡ መሄድ እንፈልጋለን ግን ይደክመናል፡፡ ወደፊት መራመድና ነገሮችን መፈፀም ያቅተናል፡፡ ይህ እንግዳ ነገር አይደለም ፡፡ የሰው ጉልበት ያልቃል፡፡ ብርቱና ሃያል ሰው እንኳን ይደክማል ይታክታል፡፡ እግዚአብሄርም ስለዚህ እንዲህ ይላል፡፡
ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ ኢሳያስ 40፡30
እግዚአብሄር ሊያድሰን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ ማደስ ማስነሳት ልማዱ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለደካማ ሃይልን መስጠት ይወዳል፡፡ እግዚአብሄር ብርታት ለሌለው ጉልበትን በደስታ ይጨምራል፡፡
ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ኢሳያስ 40፡29
የማይደክመው እግዚአብሄር አምላካችን ሆኖ ሁልጊዜ እንበረታለን፡፡ ከማይደክመውና ከማይታክተው ከሃያሉ ከእግዚአብሄር ጋር ተገናኝተን የሚጎድልብንና የምናጣው ምንም ሃይል የለም፡፡
አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።
ሂድ አድርግ አትቁም አትዘግይ የሚሉ በራሳችን እንድንራመድ የሚያጣድፉ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር እግዚአብሄርን በመተማመን መጠበቅ ነው፡፡ ጊዜ ያለፈብን ሊመስለን ይችላል፡፡ የተበለጥን ሊመስለን ይችላል፡፡ የሳትን ሊመስለን ይችላል፡፡ ማስተዋሉ የማይመረመረውን እግዚአብሄርን በመጠበቀ የምናጣውና የሚጎድልብን ነገር የለም፡፡
እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳያስ 40፡31
በራስህ ትደክማለህ ትካክታለህ፡፡ እግዚአብሄር ሲያድስ ግን ሄደህ ሄደህ አትደክምም፡፡ ሮጠህ ሮጠህ አትታክትም፡፡ እግዚአብሄር እድሳት ከፍ ያደርግሃል ከሁኔታው ሁሉ በላይ ያወጣሃል፡፡ ስለዚህ በምናደርገው ሁሉ እግዘዚአብሄርን በመተማመን እንጠብቅ፡፡ ለእግዚአብሄ እድሳት ስፍራ እንስጥ፡፡ እግዚአብሄርን በመጠባበቅ እንዲያድሰን እንፍቀድለት፡፡
ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳያስ 40፡27-31
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መጠበቅ #በመተማመን #ያድሳሉ #ይወጣሉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment