በክርስትና ህይወታችን አድገን አድገን የመጨረሻው የስኬትና የብልፅግና ደረጃ ምን እንደሆነ ማወቅ ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ስንደርስ እንድናውቀውና እንድንረካ "ይሄ ነው" እንድንል ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡
ስለዚህ ደረጃ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ አስተያየት አላቸው፡፡ ይህንን ሁሉ አስተያየት ብንሰማ እንስታለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚለውን ከሰማን ግን እናርፋለን፡፡
የክርስትና ህይወት ግቡ ምንድነው? የክርስትና ህይወት የስኬት ጣራው ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ሊመልስልን ሙሉ ስልጣን ያለው የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ደግሞ እውነት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ኦሪጂናል የእግዚአብሄር ሃሳብና ፈቃድ ነው፡፡
የእግዚአብሄር ሰው ደረሰበት የሚባለው ምን ሲኖረው ነው? የጌታ ሰው እንደው ህይወቱ ሲያስቀና የሚያስብለው ምንና ምን ሲኖረው ነው? የሚለውን ጥያቄ መፅሃፍ ቅዱስ በሚገባ ይመልሰዋል፡፡
ክርስቲያን በለፀገ የሚባለው ሚሊየነር ሲሆን አይደለም፡፡ ክርስቲያን ተሳካለት ደረሰበት የሚባለው ዝነኛ ሲሆን አይደለም፡፡
ክርስቲያን ደረሰበት ይህ የተሳካለት ሰው ነው የሚባለው መሰረታዊ ፍላጎቱን አሟልቶ ጌታን ሲከተል ነው፡፡ ክርስቲያን ደረሰበት የሚባለው እግዚአብሄር በህይወቱ ላስቀመጠው ሃላፊነት የሚያስፈልገው ነገር ካልጎደለበት ነው፡፡ ክርስቲያን ተሳካለት የሚባለው ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ፍላጎት ካሟላ ነው፡፡
ጌታ ከመከተል የተሻለ የስኬት ደረጃ የለም፡፡ ጌታን ከመውደድ ያለፈ የብልፅግና ደረጃ የለም፡፡ ጌታን ከማምለክና እግዚአብሄርን ከመምሰል የላቀ የስምረት ደረጃ የለም፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6-8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment