Popular Posts

Thursday, October 13, 2016

በሁሉ አመስግኑ

ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡16-18

በሁሉ አመስግኑ የሚለው አባባል ለስጋችን ቀላል አይደለም፡፡ በሁሉ አመስግኑ የሚለው በቃሉ የተሰጠንን ደረጃችንን ትተን ሁሉንም እንድቀበል እየተጠየቅን አይደለም፡፡
እኛ በክርስትና ቃሉ እንድንጠብቀው የሰጠን የህይወት ደረጃ አለን፡፡ ሁሉንም እንዳመጣ የምንቀበል ሰዎች አይደለንም፡፡ የምንቀበለው ነገር አለ የማንቀበለው የምንቃወመው ነገር ደግሞ አለ፡፡
በሁሉ አመስግኑ ሲል ታዲያ ምን ማለቱ ነው የሚለውን መረዳት ይህን ቃል በሚገባ እንድንታዘዘው ይረዳናል፡፡ በሁሉ አመስግኑ ምን ማለት እንደሆነና እንዳልሆነ ካወቅን ከምን አንፃር እንደምናመሰግን መረዳትን እናገኛለን፡፡
በሁሉ ማመስገን ያለብን ሰባት ምክኒያቶች ፡-
  • · በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ የተሸነፉ ሰዎች ንግግር ሊመስል ይችላል፡፡ እኛ እግዚአብሄር አይደለንም፡፡ እንደ ሰውነታችን አቅማችን የሚፈቅደውን ነገር ሁሉ ካደረግን በኋላና ሃላፊነታችንን ከተወጣን በኋላ ከዚያ አልፎ የሚመጣውን በፀጋ የመቀበል ጥሪ ነው ፡፡
መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ሐዋርያት 27፡15
  • · በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ መሞከር ያቆሙ ሰዎች ንግግር ሊመስል ይችላል፡፡ በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ ለመታዘዝ በራስ ማስተዋልና ችሎታ አለመታመንና በእግዚአብሄር ሁሉን አዋቂነት ላይ መደገፍን ይጠይቃል፡፡ ነገሮች ከእኛ እጅ የወጡ ሲመስለን በሁሉ ልናመሰግን የምንችለው ከእግዚአብሄር እጅ ግን እንዳልወጡ ስናስተውል ብቻ ነው፡፡
አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ኢሳይያስ 40፡28-29
  • · በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ ፈቃዳችንን ለእግዚአብሄር ፈቃድ የምናስገዛበት መንገድ ነው፡፡ ኢየሱስ ወደሞት በሚሄድበት ጊዜ አባት ሆይ ቢቻልህ ይህ ፅዋ ከእኔ ይለፍ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን ያንተ ፈቃድ ይሁን በማለት ፈቃዱን ለእግዚአብሄር ፈቃድ ያስገዛበትን ንግግር እንመለከታለን፡፡ በሁሉ አመስግኑ የእኔ ፈቃድ አይሁን ያንተ ፈቃድ ይሁን ብለን ራሳችንን የምናስገዛበት ትእዛዝ ነው፡፡
አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። ማርቆስ 14፡36
  • · በሁሉ አመስግኑ የሚለው ቃል ወደፊታችንን በእግዚአብሄር እጅ የምናስቀምጥበት ትእዛዝ ነው፡፡ በምድር ላይ ስንኖር ሁሉንም አናውቅም፡፡ እግዚአብሄር ግን ሁሉን ያውቃል፡፡ በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ ታዲያ ሁሉን ከማናውቅበት ከእኛ ክልል ወጥተን ሁሉን በሚያውቀው በእግዚአብሄር የእውቀት ችሎታ ላይ የመደገፍ ጥሪ ነው፡፡
ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ኢዮብ 42፡1-2
  • · በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ የሚያመለክተው ቸልተኝነትን ሳይሆን ነፍሱን ስለእኔ የሚተዋት ያገኛታል የሚለውን የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምንፈፅምበት የትጋት መንገድ ነው፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሉቃስ 9፡24
  • · በሁሉ አመስግኑ የሚለው ትእዛዝ በህይወት ተስፋ የቆረጡ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ንግግር አይደለም፡፡ ነገር ግን በሁሉ አመስግኑ ማለት በራሳችሁ ጉልበትና አቅም ተስፋ ቁረጡ በእግዚአብሄር ችሎታ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተደገፉ ማለት ነው፡፡ በሁሉ አመስግኑ ማለት እንዲያውም ተስፋ አትቁረጡ ማለት ነው፡፡
በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ሮሜ 12፡12
  • · በሁሉ አመስግኑ ማለት በሰው ክንድ ላይ ከመደገፍ ወጥተን ለእግዚአብሄር ስፍራ የመስጠትን ጥበብ ያሳያል፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው። ዘዳግም 29፡29
ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡16-18
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #አመስግኑ #መዳን #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #አብርሃም #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

No comments:

Post a Comment