ጌታ ኢየሱስን ከተቀበልንበት ጊዜ አንስቶ የእግዚአብሄር መንፈስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ በእኛ ውስጥ ያለው ሊያስተምረን ፣ ሊረዳንና ሊመራን ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ ያለው ጥበብን ሊሰጠንና ከከበቡን ሁኔታዎች ሁሉ በላይ እንድንሆን ሊመራን ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ በውስጣችን ያለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በሚገባ እንድታዘዝ ሊያስታጥቀን ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ያለው ሊያፅናናን ፣ መንገዳችንን ሊያደላድል ከሁኔታዎቸ በላይ እንድንሄድ ሊያመቻችልን ነው፡፡ ይህን እጅግ ጠቃሚ መንፈስ ፍሬያማ እንዳያደርገን ማጥፋት የለብንም፡፡
መንፈስን አታጥፉ፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡19
ለእግዚአብሄር መንፈስ እውቅና መስጠትና ከሚያሳዝነው ነገሮች ራሳችንን መጠበቅ መንገዳችን ስኬታማ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የእግዚአብሄርን መንፈስ ማሳዘን ደግሞ መንገዳችን እንዳይቀናና ፍሬያማ እንዳንሆን ያደርጋል፡፡
ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። ኤፌሶን 4፡25-31
የእግዚአብሄር መንፈስን የሚያዝንባቸው ነገሮች ፡-
- · ይቅር አለማለት ፣ መራርነት ፣ አለመተውና በምህረትና ርህራሄ አለመመላለስ
ለዘላለም ከእግዚአብሄር ከመለያየት በእግዚአብሄር ይቅር እንደተባለ የሚያውቅ ሰው ይቅር ለማለት አይቸግረውም፡፡ ነገሮችን መያዝና አለመልቀቅ፡፡ ሰው ሊበድለኝ በፍፁም አይገባም ፣ መበደል የለብኝም የሚል አጉል ትምክት፡ እኔነት ፡ ትእቢት የእግዚአብሄርን መንፈስ ያሳዝናል፡፡
እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። ኤፌሶን 4፡32
- · ንዴት ቁጣ ጩኸት
በስጋ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር መሞከር ፡ የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ አይሰራም፡፡ ስጋን ሁኔታዎችን በራሱ ለመቆጣጠር ያለው ጥረት፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን በእግዚአብሄር መታመንና እግዚአብሄር ነገሮችን እንዲቆጣጠር መፍቀድና መልቀቅ አይፈልግም፡፡ ቁጣና ጩኸት ለእግዚአብሄር ስፍራንና እድልን አለመስጠት ሲሆን ነገሮችን በራስ ለማቆጣጠር መሞከር ነው፡፡
መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። ኤፌሶን 4፡31
- · ውሸት
ውሸት ሰዎችን በተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ውሳኔ እንዲወስኑ ማሳሳት ነው፡፡ ውሸት በእግዚአብሄር ያለመታመን ማረጋገጫ ነው፡፡ ውሸት የሰው በረከት በእግዚአብሄር እጅ እንጂ በሰው እጅ እንደሌለ አለመረዳት ነው፡፡ ውሸት እግዚአብሄርን እንደ በረከት ምንጭ አለማወቅ ነው፡፡ ውሸት ከእግዚአብሄር ሳይሆን ከሰው መፍትሄን መፈለግ ነው፡፡
- · ምኞት
እግዚአብሄር መሰረታዊ ፍላጎታችንን እንደሚያሟላ ካላመንንና ሁል ጊዜ የጎረቤታችንን ቤት የምንመኝ ከሆንን መንፈስ እንደወላጅ ያዝናል፡፡ እግዚአብሄር የእኛን መሰረታዊ ፍላጎት ለማማላትና ምንም እንዳይጎድለን በትጋት እየሰራ ነው፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሄርን አቅርቦት እውቅና አለመስጠትና በእግዚአብሄር አሰራር አለመርካት መንፈሱን ያሳዝነዋል፡፡
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፦ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ዕብራውያን 3፡7-9
- · ማጉረምረም አለማመስገን በምንም ነገር አለመርካት ሁልጊዜ ጉድለትን ማየትና ጉድለትን ማጋነን፡፡ ምስጋና ቢስ መሆን የተደረገለትን አለመቁጠር፡፡
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10-11
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #መዳን #እምነት #መንንፈስንአታጥፉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #መንፈስ #መንፈስቅዱስ
No comments:
Post a Comment