ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ምሳሌ 29፡18
እኛ ሰዎች በጣም ውስን ነን፡፡ በአንድ ጊዜ ማድረግ የምንችለው አንድን ነገር ብቻ ነው፡፡ በአንዴ ብዙ ስራዎችን መስራት አንችልም፡፡በእኛ ውስጥ ያለው ፀጋና ሃይል እግዚአብሄር ለጠራን ስራ ብቻ የሚበቃ ነው፡፡ ይህን በውስጣችን ያለውን ፀጋ ተጠቅመን ውጤታማ መሆን የምንችለው እግዚአብሄር በምድር ላይ ለምን እንደፈለገን ስንረዳ ብቻ ነው፡፡
ውጤታማ ለመሆን እግዚአብሄር የጠራንን ያንን አንዱን ነገር ብቻ ነው ማድረግ ያለብን፡፡ የምናደርገውን ነገር ደግሞ እኛ አንመርጥም፡፡ እንድንሰራው የፈለገውን የሚያውቀው ለምን እንደጠራን የሚነግረን እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ ነው እግዚአብሄር የጠራንን ጥሪ ከእግዚአብሄ ፈልገን ማግኘትና በዚያ በጠራን ብቻ ላይ ማተኮር ያለብን፡፡
ለዚህ ምሳሌ ሊሆንልን የሚችለው ኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ሲኖር እግዚአብሄር አብ ለምን እንደፈለገውና ለምን እንደጠራው ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡
ጲላጦስም፦ እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ዮሃንስ 18፡37
ኢየሱስ በምድር ላይ ለምን እንደመጣ ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ከራእዩ ጋራ የማይሄዱ ነገሮችን ላለማድረግ እጅግ ይጠነቀቅ ነበር፡፡ ኢየሱስ ለምን እንደተሾመ ብቻ ሳይሆን ለምን እንዳልተሾመም ጭምር ጠንቅቆ ተረድቶ ነበር፡፡
ከሕዝቡም አንድ ሰው፦ መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው። እርሱም፦ አንተ ሰው፥ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ አንድሆን ማን ሾመኝ? አለው። ሉቃስ 12፡13-14
ኢየሱስ ለምን እንዳልተጠራ ጥርት ያለ ራእይ ስለነበረው በአገልግሎቱ የተደነቁ ሰዎች ሊያነግሱት ሲሞክሩ ፈቀቅ እንዳለ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ። ዮሃንስ 6፡15
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ስለእርሱ እንደተፃፈው ሊፈፅም ነበር፡፡ እግዚአብሄር ያየለትን ሃላፊነት ሊወጣ ነበር ኢየሱስ ወደምድር የመጣው፡፡
በዚያን ጊዜ፦ እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል። ዕብራውያን 10፡7
እግዚአብሄር ያዘጋጀለት ነገር ሁሉ ለራእዩ ማስፈፀሚያ ታስቦ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፦ መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ ዕብራዊያን 10፡5
ባለራእይ የሚንቃቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉና ወደ ራእዩ ለመሄድ የማይረዱትን ወይም የሚያደናቅፉትን ነገሮች እየናቀ እንደሚሄድ የባለ ራእዩ ከኢየሱስ ህይወት እንመለከታለን፡፡
እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ራዕይ #ምሪት #የእግዚአብሄርአጀንዳ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment