ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29፣31
እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው ሙሉ አድርጎ ነው፡፡ አዳም ምንም የማይጎድለው ሙሉ ተደርጎ ነው የተፈጠረው፡፡ አዳም በምድር ላይ ተቋቁሞ ለመኖር ሚስት አላስፈለገውም፡፡ አዳም ካለሚስት በራሱ ሙሉ ነበረ፡፡ አዳም በራሱ ከእግዚአብሄር ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው፡፡ አዳም በራሱ እግዚአብሄርን የሚያምን ከእግዚአብሄር ጠይቆ የሚቀበል ነበረ፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሄርን ሰውን ከፈጠረ በኋላ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ የሚለው፡፡
እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን። ዘፍጥረት 1፡31
ሰው ከማግባቱ በፊት ሙሉ እንደነበረና በእግዚአብሄር ላይ ሙሉ ለሙሉ ይደገፍ እንደነበረ ሁሉ ካገባም በኋላ ሙሉ ለሙሉ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ አለበት፡፡ ሰው ሚስት ሲያገባ በእግዚአብሄር ላይ ያለውን መደገፍ በሚስት ላይ ባለ መደገፍ መለወጥ የለበትም፡፡ እንዲሁም ሴት ማግባትዋ በእግዚአብሄር ላይ ያላትን መደገፍ ፣ ከእግዚአብሄር ጋር ያላትን ግንኙነትና በእግዚአብሄር ላይ ያላትን መታመን በፍፁም መተካት የለበትም፡፡
እንዲያውም እንደዚህ ሙሉ የሆነ ሰው ብቻ ነው ሚስትን ማግባት ያለበት፡፡ እንዲሁም ከጌታ ጋር የተሳካ ግንኙነት ያላት ሴት ነች ባል ማግባት ያለባት፡፡ ጎዶሎነት ተሰምቷት ጉድለቷን ለመሙላ ባል ማግባት የምትፈልግ ሴት ሳትሆን ጌታን የምታምነው ሴት ነች ባል ማግባት ያለባት ፡፡ ከጌታ እንዴት ጠይቃ እንደምትቀበል የምታውቅ የእምነት ሴት ነች ባል ማግባት ያለባት፡፡ ስለእኔ ብሎ ቤቱን ይባርካል ብላ በጌታ ላይ የምትታመን ሴት ነች ማግባት ያለባት፡፡
አላስፈላጊ የሆነ በባል ወይም በሚስት ላይ መደገፍ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል፡፡ ስለዚህ ነው እግዚአብሄር ያገባ እንዳላገባ ይኑር በማለት ያገባ ሰው በሚስቱ ወይም ያገባች ሴት በባልዋ ላይ አላግባብ እንዳትደገፍና የሚመክርው፡፡
የዚህ አለም መልክ ጊዜዊና አላፊ በመሆኑ ከመጠን በላይ ልንደገፍበት የሚያስችል አይደለም፡፡ ስለዚህ ያገባ እንዳላገባ ወይም እንደ ብቸኛ ሰው እንዲኖር የተጠየቀው፡፡ ያገባ በማያልፈው በእግዚአብሄር ላይ ያለውን መደገፍ በሚያልፈው በሰው ላይ ባለ መደገፍ እንዳይለውጠው የሚያስጠነቅቀው፡፡
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
No comments:
Post a Comment