የመንፈስን አንድነት የምንጠብቀው በሰላም ነው፡፡ ካለሰላም የመንፈስ አንድነት ሊጠበቅ አይችልም፡፡ የአንድነት ማሰሪያው ሰላም ነው፡፡ ለአንድነት የሚያስፈልገው ሰላም ነው፡፡
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም ከሆነ አንድነት ይቀለዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄ ጋር ባለው ሰላም ከረካ ከሰው ጋር ሰላም ይሆናል፡፡ ሰው ወደ ሰው የሚሄደው ሰላምን ፈልጎ ሳይሆን ሰላምን ሊሰጥ መሆን አለበት፡፡ ለሰው ሰላምን በመስጠት ላይ ካተኮረ የሚያሰናክለው ነገር አይኖርም አንድነትንም መጠበቅ ይችላል፡፡
ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ማቴዎስ 10፡12-13
ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። ሉቃስ 10፡5-6
ትህትና ሌላው ለአንድነት ወሳኝ የሆነ ነገር ትህትና ነው፡፡ ዝቅ አለማለት ሰላምን የሚጎዳ ነገር ነው፡፡ አንድነትን የሚፈጥረው ሌላው ከእኛ እንደሚሻል መቁጠር ብቻ ነው፡፡ ሌላውን አለመቀበል የእኔ ሃሳብ ብቻ ይሁን ማለት የአንድነት ጠር ነው፡፡ ሌላውን አለመቀበልና በመናቅ አንድነትን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ሰው መለየት ከፈለገ ምኞቱን ብቻ መከተል ይበቃዋል፡፡
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፥1
ትእግስት ሁላችንም የተለያየን ሰዎች ነን፡፡ ከእኛ የተለየውን ሰው ካልታገስነው አንድነትን ልንጠብቅ አንችልም፡፡ ልዩነታችንን ካልተቀበለን ሁሉንም ሰው ጨፍልቀን ተመሳሳይ ለማድርግ ከሞከርን ሰላም ይደፈርሳል፡፡ ከማይመስሉን ሰዎች ጋር አብረን መኖር ፣ መስራትና ማገልገል ካልቻልን ሰላም ሊጠበቅ አይችልም፡፡
ይቅርታ ይቅር መባባል ሰላምን ብሎም አንድነትን ይጠብቃል፡፡ ሰው ይቅር ማለት ካልቻለ አንድነቱም መጠበቅ ያቅተዋል፡፡ ይቅር ማለት አንደነትን የመጠበቂያው መንገድ ነው፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆላስይስ 3፡13
የዋህነት ሌላው አንድነትን ለመጠበቅ አስፈላጊው ነገር የዋህነት ነው፡፡ የዋህነት ያለንን ሃይል ለክፋት አለመጠቀም ነው፡፡ የዋህ ሰው ለፍቅር ለሰላምና ለአንድነት የሚሸነፍ ሰው ነው፡፡ ተንኮል በሌለበት ፣ ሁለት ሃሳብ በሌለውና የሚናገረውና የሚያስበው አንድ በሆነ ሰው ሰላም ይጠበቃል፡፡
ፍቅር ፍቅር ደግሞ ወሳኙ የአንድነት ንጥረ ነገር ነው፡፡ ሌላውን ካልተረዳነውና ከሌላው ጋር ራሳችንን ካላስተባበርን አንድነትን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ካለፍቅር አንድነት የለም፡፡ ሌላውን መውደድ ሌላውን መቀበል ሌላውን ማክበር አንድነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ 14
በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ ቆላስይስ 3፡14-15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#አንድነት #የዋህነት #ፍቅር #ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #የመንፈስአንድነት #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment