ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበላችንና በህይወታችን ላይ በመሾማችን እግዚአብሄር ልጆች አድርጎ ተቀብሎናል፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ስለሆንንና እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ስለሚሰራ ነገሮች ሁሉ ይከናወንልናል፡፡
በጌታ ኢየሱስ የመስቀል ስራ አምነው የዳኑትን ጻድቃንን መንገዳቸው ከንጋት ብርሃን ጋር ይመሳሰላል፡፡ የንጋት ብርሃን ጠቃሚና ወሳኝ ብርሃን ነው፡፡ የንጋት ብርሃን ጨለማው ማለፉንና ብሩህ ቀን መምጣቱን የሚያበስር እርግጠኛ ምልክት ነው፡፡ የንጋት ብርሃን የሙሉ ተስፋ ብርሃን ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስከሚሆን እየጨመረ እንደሚሄድ ያስተምራል፡፡ የጻድቃን መጨመር ፣ ማበብ መውጣት ፣ ማሸነፍ እርግጥ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ተገናኝቶ የሚወርድ ፣ የሚጠፋ ፣ የሚከስም ሰው የለም፡፡ ጻድቃን እየወጡና ከፍ እያሉ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
የጻድቃን መንገድ ግን እንደዱብዳ አይደለም፡፡ የጻድቃን ማበብ ድንገተኛ አይደለም፡፡ የጻድቃን መንገድ ቀስ በቀስ እየጨመረ የሚሄድ ነገር ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ በጊዜያት ውስጥ የታመነና ፀንቶ የቀጠለ ሰው እጅግ እስከሚባረክ ድረስ እንደሚባረክ ያስተምራል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
የንጋት ብርሃን ከጭላልጭልነት ጀምሮ እንደሚበረታና የቀትር ፀሃይ እስከሚሆን ቀስ በቀስ እየጨመረ እንደሚሄድ ሁሉ የጻድቃን መንገድም እንዲሁ ጥቂት በጥቂት ይጨምራል፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11
የንጋት ብርሃን ሙሉ ቀን እስከሚሆን መጨመሩን እነደማያቆም እንዲሁ የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስከሚሆን እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ የጻድቃን መንገድ ሙሉ በረከት በህይወታቸው እስከሚገለጥ ድረስ መጨመሩን አያቆምም፡፡ የጻድቃን በረከት ከመጨመር አይቆምም፡፡
የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። ምሳሌ 4፡18
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
#ኢየሱስ #ጌታ #ጻድቃን #የታመነ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ጥቂትበጥቂት #ሙሉቀን #በረከት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment