በአገራችን ስላለው የሰዎች መሞት ስናስብ ችግሩ አንድ መልስ እንደሌለው እናስተውላለን፡፡ ለጥያቄው አንድ መልስ ብቻ መመለስ አንችልም፡፡ አንዳንዱ ሰው መፀለይ ብቻ ነው መፍትሄው መናገር አያስፈልግም ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ መቃወም ነው እንጂ መፀለይ ምን ያስፈልጋል ይላል፡፡ እንደ እኔ ግን አንድ መልስ የለውም እላለሁ፡፡ ይህን የመጣውን እንደ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ መመለስ አለብን፡፡
እንደ ክርስቲያን የህዝብን እልቂት ስናይ በጣም እናዝናለን፡፡ ልባችን ይሰበራል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስም ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ ስለሚል ስለሞቱት የሃዘንተኞችን ሃዘን እንካፈላለን፡፡ ወንድማቸውን እህታቸውን አባታቸውን እናታቸውን ልጃቸውን ካጡት ጋር እናዝናለን ልባችን ያለቅሳል፡፡
ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። ሮሜ 12፡15
ይህም ብቻ አይደለም ባገኘነው አጋጣሚ በልባችን ያለውን ሃሳብ እንናገራለን፡፡ የተሳሳተውን ትክክል አይደለም እንላለን፡፡
ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥ ሉቃስ 3፡18-19
እንዲሁም እንፀልያለን፡፡ እንፀልያለን የሚለው ቃል ለአንዳንዶች የማይሰራና (passive) ገቢር እንዳይደለ ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የክርስቲያን ፀሎት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ክርስቲያንና ፀሎትን መለየት አይቻልም፡፡ ሰይጣን ስፍራን እንዳያገኝ አጥብቀን መፀለይ አለብን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ያመነ የፃዲቅ ሰው ፀሎት በስራው እጅግ ሃይል ያደርጋል፡፡
የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ያዕቆብ 5፡16-18
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4
እግዚአብሄር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን እንዲያውቁ ይወዳል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ነገ ሳንል ወንጌልን እንሰብካለን፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሃጢያት እንደሞተ የምስራቹን እንናገራለን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ተቃውሞ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment