Popular Posts

Saturday, October 22, 2016

ለመጣላት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም

መጣላትና መለያየት ብርቅ አይደለም፡፡ ሰው ለመጣላትና ለመለያየት ምክንያት አላገኘሁም ካለ ይዋሻል፡፡ ለመጣላትና ለመለያየት ምክንያት ሞልቷል፡፡ ሰው ለመለያየት ምክንያት አገኘሁ ካለ አያስደንቅም፡፡ ሰው ከእከሌ የምጠላው ነገር አለ ቢል ወይጉድ እንዴት የማይመቸው ነገር ሊያገኝ ቻለ ብሎ የሚደነቅ ሰው የለም፡፡ ከሌላው ሰው የምትጠላውና የማትወደው ከአንድ በላይ ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ለመጣላትና ለመለያየት አስተዳደጋችን ፣ ባህላችን ፣ አስተሳሰባችን ፣ አመለካከታችን ስጦታችን መለያየቱ ብቻ ይበቃል፡፡
ለመጣላት ሌላ ሰውም አያስፈልግም፡፡ ከራሳችሁ ህይወት የማትወዱት ነገር አለ፡፡ ይህ በህይወቴ ባይሆን ኖሮ የምትሉት ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ ይህን ነገር ብለውጠው ኖሮ የምትሉት ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ለመጣላት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ለመጣላት ጥረት ማድረግ  አያስፈልግም፡፡ ጥል አጠገባችሁ ነው፡፡
ህይወት ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ለመጣላት የሚያስፈልገው ለስጋችሁ ትንሽ አርነት መስጠት ብቻ ነው፡፡ ለመጣላት የሚያስፈልገው ከመጠን በላይ ዘና ማለት ብቻ ነው፡፡ ለመጣላት አንደበትን አለመግዛት በቂ ነው፡፡ ትንሽ ስንፍ በማድረግ ሳታውቁት ተጣልታችሁ ታገኛላችሁ፡፡ ካልተጠነቀቃችሁ በማይሆን ነገር ከገዛ ራሳችሁ ጋር እንኳን ተጣልታችሁ ትገኛላችሁ፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡13
ሚስት ከባልዋ የማትወደውን ነገር ቢኖራት አያስደንቅም፡፡ እንዴት ያስደንቃል? እንዲያውም የሚያስደንቀው ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ሁሉን ነገር እወድለታለሁ አንድም ነገር እንዲለውጥ አልፈልግም ካለች ነው፡፡  
አብሮ ለመስራት ግን ባህሪ ይጠይቃል፡፡ አብሮ መኖር ግን መሸከም ትህትና የዋህነት ይጠይቃል፡፡ አብሮ ለመስራት ግን መዋደድ ሃጢያትን መሸፈን ከእኛ የተለየውን ሰው መረዳት ይጠይቃል፡፡
ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 4፡8
አብሮ መስራት ስጋን መጎሸም ይጠይቃል፡፡  
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡27
በአንድነት አብሮ መስራት ንቃትና በመጠኑ መኖርን ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡
በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡13-14
ለዲያቢሎስ ስፍራን ላለመስጠት ትምክትን ዋጥ አድርጎ በአንድነት መኖርና በአንድነት መስራትን ይጠይቃል፡፡ ለአንድ አላማ ለመስራት ትጋትን ይጠይቃል፡፡
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #መለያየት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment