እግዚአብሄር ይመስገን ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ ይህንን ንግግር ስናገር ሰዎች በአንድ አቅጣጫ ብቻ ስለሚመለከቱት ህልሜ ውስንና ትንሽ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ህልሜን እየኖርኩት ነው ስል ማለም እንዳቆምኩኝና ህልሜ ያለቀ ይመስላቸዋል፡፡ ህልሜን አየኖርኩት ነው ስል አንዳንዶች ተስፋ የቆረጥኩ ከዚህ በላይ ማየት ያቃተኝም ሁሉ ይመስላቸዋል፡፡
በፍፁም አይደለም፡፡ ህልሜን እየኖርኩት ነው ስል ምን ማለቴ እንደሆነ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ አሁን ያለኝ ነገር ሁሉ የእኔ አይደለም፡፡ አሁን ያለኝ ነገር እኔጋ ስለቆየ የእኔ እንደሆነ አላስብም፡፡ አሁን ያለኝ ነገር ሁሉ ከእግዚአብሄር የተቀበልኩት ነው እንጂ የእኔ አይደለም፡፡
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ቆሮንቶስ 4፡7
ስለዚህ ህልሜን እየኖርኩት ነው ስል እግዚአብሄ ታማኝ አምላክ ነው እንደተራራ የከበደብኝን ነገር እርሱ ራሱ አድርጎልኛል ማለቴ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ አሁን የደረስኩበት ደረጃ ከአመታት በፊት ተራራ ሆኖብኝ የነበረ መንፈሳዊ ደረጃ ነው፡፡ አሁን ያለሁበት የአገልግሎት ደረጃ ላይ እንደምደርስ እኔን ለማሳመን እግዚአብሔር ብዙ ቃል መጠቀም ነበረበት፡፡ እግዚአብሄር ተስፋ ስቆርጥ አፅናንቶኛል፡፡ ህልሜን ለመጣል ስፈተን ይቻላል ይደረስበታል ብሎ አበረታቶኛል፡፡
ዳዊትን ከበግ እረኝነት ወደንግስና ያመጣው እግዚአብሄር ነው፡፡ ህልሙን እየኖረ እያለ እግዚአብሄር ከተጨማሪ ህልሞች ጋር ወደእርሱ ሲመጣ እግዚአብሄርን እየኖረ ስላለው ህልምና ሊፈፀም ስላለው ህልም አመሰገነ፡፡
ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? 2ኛ ሳሙኤል 7፡18
ስለዚህ ነው ህልሜን እየኖርኩት ነው የምለው፡፡ በፊት ያልነበረኝ አሁን የደረስኩበት የህይወትና የአገልግሎት ደረጃ ሰላለ ነው ህልሜን እየኖርኩት ነው የምለው፡፡
ሶስተኛ እግዚአብሄር ስለዚህ ስለደረስኩበት ደረጃ ሊመሰገን ስለሚገባው ነው፡፡ ይህ ማለት ከአሁን በኋላ ምንም ህልም የለኝም ማለት ግን አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሄርን ስለደረሱበት ማመስገን የማይፈልጉት ሌላ የሚፈልጉት ነገር የሌለ ይመስልብናል ብለው በማሰብ ነው፡፡ ህልምን መኖርና ሌላ ህልም ማለም አብረው የሚሄዱ እንዲያውም የአንዱ እምነት ለሌላው ምስክር የሚሆንበት እንጂ የሚቃረኑ አይደሉም፡፡
አሁንም ብዙ የሚፈፀሙ ህልሞች አሉኝ፡፡ ወደፊት የማያያቸው ብዙ ደረጃዎች አሉኝ፡፡ ብዙ የምደርስባቸው ግቦች አሉኝ፡፡
ልደርስባቸው የምዘረጋባቸው ህልሞች ከፊቴ አሉ ማለት ግን አሁን የምኖረውን ኑሮና የመንፈሳዊ ህይወት ደረጃ ስለደረስኩበትር ብቻ አጣጥለዋለሁ ማለት አይደለም፡፡ የወደፊት ህልም አለኝ ማለት አሁን ስለደረስኩበት ጌታን አላመሰግንም ማለት አይደለም፡፡ ወደፊት ህልም አለኝ ማለት በደረስኩበት ህልም አልደሰትም ማለት አይደለም፡፡
የአሁኑም የህይወቴ ደረጃ ፣ አሁን በክርስቶስ ያለኝ የነፃነት ደረጃ ፣ አሁን ያለኝ መንፈሳዊ አርነት ፣ አሁን ያለኝ የአገልግሎት ደረጃ አንድ ቀን የፀለይኩበት ፣ አንድ ቀን በእጅጉ የፈለኩት ፣ አንድ ቀን ያወጅኩትና አንድ ቀን እንደተራራ የሆነብኝ ደረጃ ነበር፡፡
ስለእናንተን አላውቅም እኔ ግን ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ እግዚአብሄ ይመስገን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #ህልም #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment