ሰው ሁሉ እንዲድንና እውነቱን ወደማወቅ እንዲደርስ የእግዚአብሄር ይወዳል፡፡ የዳንነው ሁላችን ደግሞ የዳነው እንድናገለግለው ነው፡፡ እንደ ክርስትያንነታችን ሁላችንም የምናደርጋቸው የጋራ ነገሮች ቢኖሩም በተለይ ደግሞ ለእያንዳንዳችን የተለየ ጥሪን በህይወታችን አስቀምጧል፡፡ እያንዳንዳችን ውስን በመሆናችን ሁላችንም ለሁሉም ነገር አልተጠራንም፡፡ ከሌሎች በተለየ መልኩ ጥሩ አድርገን የምንሰራው የተለየ ጥሪ አለን፡፡
እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን ማወቅ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን ስናውቅ ጥሪያችንን ብቻ በማድረግ እንረካለን፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን ስናውቅ ለምን እንዳልጠራንም ስለምናውቅ እናርፋለን፡፡ እግዚአብሄር የጠራንን ጥሪ ስንለይ ካለ አስፈላጊ ፉክክር ነፃ እንወጣለን፡፡
እግዚአብሄር ለምን እንንደጠራን ስናውቅ ራሳችንን ስራችንን አገልግሎታችንን የምንለካው እግዚአብሄር በህይወታችን ካስቀመጠው ጥሪ አንፃር ብቻ ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን ስናውቅ እግዚአብሄር የሰጠንን ሃይልና ጉልበት በአላስፈላጊ ነገር ላይ ከማባከን እንድናለን፡፡ እግዚአብሄር ለምን ወደዚህ ምድር እንዳመጣን ስናውቅ ያንን ሰርተን በምድር ጌታን እናከብረዋለን፡፡
ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10
የእግዚአብሄር ጥሪ ማወቂያ አንድ ቀመር ወይም ፎርሙላ ባይኖረውም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የእግዚአብሄር ጥሪ እንዴት ለማወቅ እችላለሁ ለሚለው ጥያቄያችሁ የተወሰነ መልስ ሊሰጣችሁ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ እንዲሁም ጥሪያችንን መለየት ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ ስለሆነ በእግዚአብሄር ቃል ማደግ ፣ በፀሎት መቆየትና እግዚአብሄርን መታዘዝ በጊዜው ውስጥ ጥሪያችንን እንድንለይ በእጅጉ ይረዳናል፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን የምለይባቸው መንገዶች
- · ፍላጎታችን የሚያመዝንበት
በህይወታችን ያለውን ጥሪ የምንለየው እግዚአብሄር በልባችን ያስቀመጠውን ፍላጎት በመመልከት ነው፡፡ ልባችን ወዴት እንደሚያዘነብል በመሰለል ጥሪያችን ምን እንደሆነ ጥሩ ሃሳብ ሊሰጠን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የተቸገረ ሰው በቀላሉ የሚታየው የተቸገረ ሰው ረድቶ የማይጠግብ እንዲያውም አገልግሎት ማለት የተቸገረ ሰው መርዳት ብቻ የሚመስለው ሰው ጥሪው ምህረት ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡
- · በቀላሉ ማድረግ የምንችለው
ሌላው እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን የምንለየው በቀላሉ ለማድረግ የምንችለውን ነገር በመለየት ነው፡፡ ከሌላው ነገር ይበልጥ እግዚአብሄር ለጠራን ነገር አእምሮዋችን ይበልጥ ይከፈታል፡፡ ሌሎች ለማድረግ የሚከብዳቸውን ነገር እኛ በቀላሉ ማድረግ ከቻልን ጥሪያችን ያ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላል፡፡
- · የተለየ ደስታ የሚሰጠን
አንድን አገልግሎት ማድረግ ከሌላው አገልግሎት ይበልጥ ደስታን የሚሰጠን ከሆነ ጥሪያችን ያ እንደሆነ አንደኛው ማረጋገጫ እንደሆነ ልናስተውል እንችላለን፡፡
- · የእግዚአብሄር መንፈስ የሚመሰክርልን
እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን ከሁሉም ነገር በላይ የሚመሰክርልን የእግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ጥሪያችንን ለመለየት የእግዚአብሄርን መንፈስ በልባችን ልንሰማው ይገባል፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን የጠራን ራሱ ሊያሳየን ስለሚገባ በፀሎት ልንጠይቀው ይገባል፡፡
- · ልባችን የሚያርፍበት
ጥሪያችን ልባችን የሚያርፍበት አገልግሎት ነው፡፡ ልክ ስናገኘው ሌላ ነገር የማያምረንና ጥሪያችንን መፈለግ የምናቆምበት አገልግሎት ጥሪያችን የሆነ አገልግሎት ይሆናል፡፡
- · እርካታን የሚሰጠን
ለምንም አይነት ክፍያ ወይም ማበረታቻ የማንሰራው ነገር ፣ ለራሳችን እርካታ ብለን የምናደርገው ነገር ፣ የማንንም ማበረታቻ ሳንጠብቅ በትጋት ልናደርገው የምንችለው እርካታን የሚሰጠን አገልግሎት ጥሪያችን ነው፡፡
- የሌሎች ምስክርነት
ሌሎች ብዙ ሰዎች ይህን አገልግሎት በአንተ ውስጥ አያለሁ ብለው የሚመሰክሩልን አገልግሎት ጥሪያችን ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሄር በተለየ ለምን እንደጠራን እስከምናውቅ ድረስ እግዚአብሄር በከፈተልን አገልግሎት ገብተን እግዚአብሄርንና የእግዚአብሄርን ህዝብ ማገልገል ይኖርናል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጥሪ #ምስክር #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment