እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው የፈጠረው እስከ ሙሉ ስልጣን ነበር፡፡ ሰው የተፈጠረው በምድር ላይ ሙሉ ለሙሉ እንዲገዛ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ ዘፍጥረት 1፡28
በሃጢያት ምክኒያት ሰው ከእግዚአብሄር ቤተሰብነት ክብርና ስልጣን ወደቀ፡፡በዚህ ምክኒያት የአዳም ዘር ሰው ሁሉ የመግዛት ስልጣኑን አጣ፡፡ አዳም በሃጢያት ምክኒያት የገዢነት ስልጣኑን ተነጠቀ፡፡ አዳም ሃጢያት በመስራቱና ስልጣኑን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጠ፡፡
ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ሮሜ 3፡23
ስለዚህ የሰው ልጅ በእግዚአብሄር ላይ በማመፅ ስልጣኑን ለሰይጣን በመስጠቱ የሰይጣን ተገዢ ባሪያ ሆነ፡፡ በሰው በኩል ስልጣን ወደሰይጣን በመተላለፉ የተነሳ ኢየሱስ በሰው አምሳል መጥቶ ሰይጣንን ድል በመንሳት ስልጣኑን ለሰው ልጅ መልሷል፡፡
ኢየሱስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ለሰው ልጅ መፍትሄ ሊሰጥ ስለመጣ የኢየሱስ ተልእኮ ሰይጣንን ድል በመንሳት ከዚህ በኋላ ጠላት በአማኞች ላይ ስልጣን እንዳይኖረው ማድረግ ነበር፡፡ ኢየሱስ ሰይጣንን ድል የነሳው ለራሱ ሳይሆን ለእኛ በእኛ ምትክ ነው፡፡
እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራውያን 2፡14-15
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።ቆላስይስ 2፡15
ኢየሱስን ስንቀበለው ኢየሱስ በልባችን መኖር ይጀምራል፡፡ በምድር ሲመላለስ ሰይጣንን ድል የነሳው ኢየሱስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ ሰይጣንን ድል የነሳው ኢየሱስ በእኛ ህይወት የሰይጣንን መሸነፍ ሊያፀና በልባችን ይኖራል፡፡
ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡10
አሁን ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን የህይወቱ ጌታ አድርጎ ሲቀበል የልጅነት ስልጣኑ ይመለሳል፡፡ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
የኢየሱስ አማኝ የሆነ ሰው ሁሉ በሰይጣን ላይት ሙሉ ስልጣን አለው፡፡ እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10፡18-19
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ዲያቢሎስ #ጠላት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ድልየተነሳ #የተሸነፈ #በረከት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment