ክርስትና የህይወት ጉዳይ ነው፡፡ ክርስትና ለሞተልን ለእየሱስ እና ለእርሱ ብቻ መኖር ነው፡፡ ታዲያ የአማኝ ክርስቲያን ምልክቱ ምንድነው? ክርስቲያን ክርስቲያንነቱ በምን ይታወቃል? አንድን ክርስቲያን በስም ብቻ ሳይሆን በእውነት ክርስቲያን የሚያደርገው ምንድነው?
ይህ ጥያቄ በህይወታችን ቸል ልንለው የማይገባ ነገር ግን በሚገባ ከልባችን ልንመልሰው የሚገባን ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ወሳኝ ጥያቄ በሚገባ መመለሳችን ህይወታችንን በከንቱ እንዳንሮጥ ይጠብቀናል፡፡
የአማኝነት ምልክት ምንድነው? የክርስቲያንነታችን እውነተኛ መለያ ምንድነው?
እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡5-8
የክርስትናችን ምልክት እምነታችን ነው፡፡ ክርስትናችን በልብሳችን ክርስትናችን አንገታችን ላይ በምናደርገው ምልክት ምልክት አይታወቅም፡፡
የክርስትና እምነታችን ደግሞ የሚታየው በአኗኗራችን ነው፡፡ የአማኝ ክርስቲያን ምልክቱ ለጊዜው በምድር ላይ ሲኖር ወደ መንግስተ ሰማያት እሰከሚሄድ ድረስ ከጌታ እየሱስ ተለይቶ በስደተኝነት እንደሚኖር ማወቁ ነው፡፡ የአማኝ ምልክቱ የስደተኛ ኑሮ ነው፡፡
ሰው ግን በምድር ላይ ሲኖር የሚፈራው አምላክ እንደሌለው እንደ ልቡ በራሱ ላይ ራሱ ጌታ ሆኖ በራሱ መንገድ የሚኖር ከሆነ የአማኝነት ማተብ የለውም፡፡
ሰው ግን በምድር ላይ ሲኖር ዛሬ ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡32) በሚል አስተሳሰብ የሚኖር ከሆነ አማኝ አይደለም፡፡
ሰው ግን በምድር ሲሆን እንደ እንግዳና መጻተኛ የማይኖርና በአለም ክፉ ውድድር ውስጥ ገብቶ በአለም ስጋዊ ምኞት የሚኖር ከሆነ አልታመነም፡፡
ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡11
ሰው ግን በምድር ሲኖር ምድር ጊዜያዊ ብቻ መኖሪያው እንደሆነ ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚሄድ በእግዚአብሄር ፊት እንደሚቀርብና እንደሚጠየቅ አድርጎ እግዚአብሄርን በመፍራት ካልኖረ የክርስትና ማተብ የለውም፡፡
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ፊልጵስዩስ 3፡19-20
መፅሃፍ ቅዱስ በእምነታቸው ስለተመሰከረላቸው ስለእምነት አባቶች ሲናገር በዕብራዊያን መፅሃፍ ላይ እንዲህ ይለናል፡፡
እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። ዕብራውያን 11፡13
No comments:
Post a Comment