Popular Posts

Tuesday, June 21, 2016

ጥበብ ሀ ሁ

የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። ምሳሌ 1፡7
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለራሱ ክብር ነው ፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ፈጣሪነትና ባለቤትነት እውቅና መስጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው ፡፡ ይህን ብቻ ሳይሆን ሰው ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት መኖር እንዳለበት ማወቅ ለሰው ልጅ ህይወት እውነተኛ ስኬት መሰረት ነው፡፡
ሰው ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ከተስተካከለ ከሌላ ከምንም ነገር ጋር ያለው ግንኙነት ሊስተካከል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰው ከፈጣሪው ጋር ያለው ግንኙነት ከተበላሸ ሌላ ምንም ነገር ሊሰምርለት አይችልም፡፡
ሰው በምድር ላይ በስጋ ለመኖርና በመንፈሳዊው አለም በነፍሱ በሚገባ ለመኖር እውቀትና ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ብዙ የእውቀትና የጥበብ አይነቶች ያሉ ሲሆን ለእያንዳንዱ የጥበብ አይነት መሰረቱ ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚኖረው ግንኙነት እውቀት ነው፡፡
ሰው ከምንም ነገር ጋር ያለውን ግንኙነትን እንዴት ማስኬድ እንዳለበት ቢያውቅ ነገር ግን ከእግዚአብሄር ጋር ስላለው ግንኙነት ጥበብ የጎደለው አላዋቂ ቢሆን ጥበቡ መሰረት እንደሌለው ቤት ለምንም ነገር ዋጋ የሌለው ይሆናል፡፡
ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥ ሮሜ 1፡21-22
ለእግዚአብሄር የሚገባውን ስፍራ መስጠትና ለእግዚአብሄር አምላክነት እውቅና መስጠት የጥበብ መሰረት ነው፡፡ የጥበብ ሀሁ እግዚአብሄርን መፍራት ነው፡፡ ካለ ጥበብ ሀሁ የጥበብ አቡጊዳም ሆነ የጥበብ መልክተ ሊኖር አይችልም፡፡
በምድር ላይ በስኬት ለመኖር ዝቅተኛው መመዘኛ እግዚአብሄርን መፍራት ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፍራት ከሞላ ጎደል ሁሉም መመዘኛ ነው፡፡ ይህ ዝቅተኛው መመዘኛ የጎደለው ሰው ምንም መመዘኛ እንዳላሟላ ይቆጠራል፡፡ ይህ ዝቅተኛውን መመዘኛ ያሟላ ሰው ግን ሌሎች ሰዎች የሚመኩባቸው ጥበቦች ቢጎሉትም ህይወቱ ይሰምራል፡፡ ይህ ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ጥበብ ጎድሎት የሚሳካለት ሰው ግን የለም፡፡
የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና። መክብብ 12፡13-14
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ምሳሌ 1፡7

No comments:

Post a Comment