Popular Posts

Follow by Email

Sunday, June 19, 2016

አባት ሁን

እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥር ሰው እንዲበዛ እንዲባዛም አዟል፡፡ እግዚአብሄር ሰውን እንዲበዛ ያዘዘው በቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡
እግዚአብሄር ያቀደው ልጅ በአባትና በእናት የማያቋርጥ የፍቅር እንክብካቤ ተሞልቶና ተኮትኩቶ እንዲያድግ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ልጅ ያሳደጉት የአባቱና የእናቱ የፍቅር ግብአት ውጤት ነው የሚባለው፡፡
ልጅ በአባትና በእናት መካከል ባለ የመጨረሻው የፍቅር ግንኙነት እንዲወለድና በእናትና በአባት አማካኝነትና በእነርሱ መካከል እንዲያድግ እግዚአብሄር ያቀደው ለልጁ በቅርበት እንክብካቤ እንዲያደርጉለትና የቅርብ የህይወት ምሳሌ እንዲሆኑለት በማቀድ ነው፡፡
አንዳንድ ሰው ግን በቸልተኝነትና በራስ ወዳድነት ይህንን የአባትነት ሃላፊነት ቸል ሲልና ይህን አላማ ሲጥስ በዚህ ምክኒያት በምድር ላይ ብዙ ችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል፡፡
በተለይ በምድር ላይ ያሉ የተለያዩ የአለማችንን ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈጠሩት ወይም የሚባባሱት በልጅነታቸው እግዚአብሄር በቤተሰብ ውስጥ ያቀደላቸውን የሚገባቸውን የአባትነት ፍቅርና ርህራሄ ተነፍገው ባደጉ ሰዎች ነው፡፡
በአባት ስርአትና ዲሲፒሊን ተኮትኩቶ ያላደገ ልጅ ሃላፊነትን ሊወስድ የሚችል ሙሉ ሰው መሆን ይቸግረዋል፡፡ ስለዚህ ነው በአለም ላይ ያሉ ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም መንስኤው የአባት በልጅ ላይ ያለ ኢንቨስትመንት ጉድለት ነው የሚባለው፡፡
ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፥ መሞቱንም አትሻ። ምሳሌ 19፡18
አባት ልጅ መውለዱን ልጅን ወደዚህ ለማምጣት ምክኒያት መሆኑን ብቻ ካየና ወደዚህ አለም ያመጣውን ልጁን ኮትኩቶና አርሞ የማሳደግ ሃላፊነት የማይወስድ ከሆነና ለራሱ ብቻ የሚኖር ራስ ወዳድ ከሆነ ልጁ በኣባትነት እንክብካቤ እጦት ይሰቃያል፡፡ በዚያም ምክኒያት ልጁ ሃላፊነትን ሊወስድ የሚችል በተራው ልጅን ወልዶ በስርአት የሚያሳድግ ዜጋ መሆን ይሳነዋል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በቤተክርስቲያን መሪነት ሃላፊነት ስለሚሰጠው መሪ መመዘኛ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡4
ስለዚህ ራስ ወዳድ ያልሆኑ ፡ ልጆቻቸውን ሳያስቆጡዋቸው በትግስትና በትጋት የሚመክሩና የሚያደሳድጉ ለቤተሰብ መታነፅ በትጋር የሚሰሩ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡ አዎን ለልጆቻቸው እግዚአብሄርን ስለመፍትራትና በቃሉ ስለመኖር መልካም ምሳሌ የሚሆኑ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡
እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። ኤፌሶን 6፡4
አባት ለገዛ ቤተሰዎቹ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ምክኒያት የአባነት እንክብካቤ ለማያገኙ ሌሎች ልጆች በቻለው መጠን ይብዛም ይነስም በህይወታቸው የአባትነትን ሚና መጫወት ይገባዋል፡፡
በተለይም ደግሞ በስጋ ያልወለዱዋቸውን ልጆች በማደጎ በማሳደግ ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ የአባትነትን ሃላፊነት የሚወስዱና በዚህ የሚያገለግሉ ሰዎች ክብር ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment