Popular Posts

Sunday, August 15, 2021

የፀሎት ያለህ የኢየሱስ ጩኸት

 


አለም በሃጢያት ጨለማ ተውጣ በነበረበት ጊዜ እና የሰውና የእግዚአብሄር ህብረት ተበላሽቶ በነበረ ጊዜ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ሊሞትልን ወደምድር መጣ፡፡ ወደምድር ሲመጣ ያየው ነገር በጣም አሰቃቂ ነበር፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ "መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው" (ዮሐንስ ወንጌል 1፡18) እንደሚል በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ ውጪ የእግዚአብሄርን ልብ እና ፈቃድ ያወቀ ማንም ሰው አልነበረም፡፡

ኢየሱስ ከእግዚአብሄር ጋር ስለነበር የእግዚአብሄርን ባለጠግነት ጠንቅቆ ያውቃል።

አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ ሮሜ 10፡12

ታዲያ ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ባለጠግነት ሲያስብ እና የሰውን ደግሞ እጦት ሲያይ ስለፀሎት ሃይል ደጋግሞ ያተምር ነበር፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላልሶ ባገለገለበት ጊዜ ሁሉ ፀሎት በእግዚአብሄር እንደሚመለስ ስለፀሎት ውጤታማነት ደግሞ ደጋግሞ አስተምሮዋል፡፡፡

ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ሙላትና እና ወደእርሱ ለሚፀልዩ ሰዎች ምን ያህል ቸር እንደሆነ ሲያስብ ስለ ፀሎት አስተምሮ ሊጠግብ አልቻለም፡፡

ኢየሱስ በፀሎት በፅናት የሚያስፈልገውን እርምጃ ሁሉ መውሰድ እንዳለብን አስተምሮዋል፡፡

ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። ማቴዎስ 7፡7

ኢየሱስ ፀሎት እንደሚመለስ በአፅንኦት ሲያስተምር እንመለከታለን፡፡

የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ማቴዎስ 7፡8

ኢየሱስ ከምድራዊ አባት በላይ መልካም አባት እንደሆነና ለሚለምኑት መልካም ስጦታን አንጂ ከመልካም ስጦታ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ሊሰጥ እንደማይችል አስተምሮዋል፡፡

ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? ማቴዎስ ወንጌል 7፡9-11

ከፀሎት ውጤታማነት አንፃር ሰው ለፀሎት የሚያስፈልገውን ጽናት ሁሉ በእምነት ማሳየት እንዳለበት አስተምሮዋል፡፡

ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? ሉቃስ 18፡1፣7-8

ፀሎት እንደሚሰራ በእግዚአብሄር ማመን እንዳለብን አስተምሮዋል፡፡

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ማርቆስ 11፡22-24

ለምነን የምንቀበለው ነገር እኛን መጥቀሙ ብቻ ሳይሆን ለምኖ መቀበል በራሱ እግዚአብሄር ምን ያህል ስለ ህይወታችን እንደሚጠነቀቅልን ስለሚያሳየን የሚያመጣው ደስታ ልዩ እንደሆነ አስተምሮዋል፡፡

በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። ዮሐንስ 16፡23-24

ፀሎታችን እንዲመለስ በእርሱ እንደተሾምን አስተምሮዋል፡፡

እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። ዮሐንስ 15፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ መጣጥፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

#እግዚአብሔር #ኢየሱስ #ለምኑ #ፀሎት #ጀብዱ #እምነት #ፍቅር #ጋብቻ #ጽናት #መታመን #ጸጋ #ማዳን #ቤተ ክርስቲያን #ምስክርነት #ደስታ #ስብከት #መጽሐፍ ቅዱስ #ማቴዎስ #አቢይዲንሳ #ቅዱሳትመጻሕፍት #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment