Popular Posts

Follow by Email

Sunday, January 8, 2017

የጌታን መንገድ አዘጋጁ

የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። ማርቆስ 1: 1-4
ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት አስቀድሞ የመጣው መጥምቁ ዮሃንስ ነበር፡፡ ዮሃንስ የመጣው ለኢየሱስ መንገድን ለመጥረግ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር የተባለው አማኑኤል ከመምጣቱ በፊትና የእግዚአብሄርን ክብር ከማየቱ በፊት የሚቀድመው የሰው ልብ ዘጋጀት ነበር፡፡
እግዚአብሄር ስራን ሲሰራ ከሰው ጋር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ክብር በሰው ህይወት እንዲገለጥ ሰው ልቡን ማዘጋጀት አለበት፡፡ እግዚአብሄር ጨዋ ነው፡፡ በማይፈልገውና በማይጠብቀው ሰው ህይወት ውስጥ በግድ አይሰራም፡፡
በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ። ሉቃስ 33-6
እግዚአብሄር ሲሰራ የሚቀበለውና አብሮት የሚሰራ ሰው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በተዘጋጁ ሰዎች ታላላቅ ስራዎችን ይሰራል፡፡ እግዚአብሄር በሚፈልጉትና በሚጠብቁት ሰዎች በሃይል ይጠቀማል፡፡ እግዚአብሄር ልባቸውን እርሱን ለመቀበል የሚያዘጋጁትን ሰዎች ሊያድንና ክብሩን ሊያሳያቸው ይመጣል፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር በህይወታቸን መገለጥ የልባችን መንገድ መጠረግና መስተካካል አለበት፡፡
ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ
እኔ ለእግዚአብሄር ማዳን አልበቃም ለሚል ሰው የምስራች አለኝ፡፡ የእግዚአብሄር ማዳን ስጦታ እንጂ ደሞዝ አይደለም፡፡ የመዳኛና  የእግዚአብሄርን ክብር በህይወታችን የማያ መንገዱ የኢየሱስን የሃጢያት መስዋእትነት እንደ ስጦታ መቀበል እንጂ በመልካም ስራ ደህንነትን መግዛት አይደለም፡፡
እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ማቴዎስ 11፡28
ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል
እኔ የእግዚአብሄር ማዳን አያስፈልገኝም፡፡ እኔ መልካም ሰው ነኝ ፡፡ የኢየሱስ መስዋእትነት አያስፈልገኝንም ፡፡ እኔ በራሴ ስራ እድናለሁ ለሚል በሚሰራው መልካም ስራ ለመዳን የሚወድ ቢኖር ትሁት እንዲሆንና የእግዚአብሄርን የማዳኛ መንገድ እንዲቀበል  ራሱን እንዲያዋርድ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡
በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ገላቲያ 5፡4
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። ኤፌሶን 2፡8-9
ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን
የእግዚአብሄርን የማዳኛ መንገድ ለመቀበል በእምነት መሆን ይጠይቃል፡፡ በብልጠትና በሰው ጥበብ የእግዚአብሄርን መንገድ አንረዳም፡፡  በእምነትና በስብከት ሞኝነት የምንቀበለው እንጂ እንዴት እንደሆነ ተመራምረን በአእምሮዋችን ብጥር አድርገን የምንረዳው አይደለም፡፡
በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡21
ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን
የእግዚአብሄር ክብር እንዲገለጥ ልባችን መዘጋጀት አለበት፡፡ ሸካራው ልባችን ለእግዚአብሄር ማዳን መስተካከልና መዘጋጀት አለበት፡፡ 
ሰው ለእግዚአብሄር ማዳን ካዘጋጀ የእግዚአብሄር ክብር ይገለጣል፡፡ የእግዚአብሄር ክብር ስጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ይገለጣል፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፡፡ ደህንነትና የእግዚአብሄርን ክብር ማየት የሚጠይቀው ልብን ለእግዚአብሄር ማዘጋጀት ብቻ ነው፡፡
ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #የእግዚአብሔርክብር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #መዳን #ማድረግ #መስዋእት #ዝግጅት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment