በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። ሮሜ 12፡4-5
መንፈሳዊ እውነትን ለማስጨበጥ ተፈጥሮአዊ አካላችን በምሳሌነት ሲጠቀስ ብዙ ጊዜ እንመለከታለን፡፡ አካላችንን በመመልከት ብቻ ብዙ መንፈሳዊ ትምህርትን ልንቀስም እንችላለን፡፡
ሃዋሪያው ጳውሎስ “ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁም “1ኛ ቆሮ 11፣14 በማለት ተፈጥሮን በመመልከት ብቻ የምንማራቸው ድንቅ ትምህርቶች እንዳሉ ያስተምረናል፡፡
ለምሳሌ የእኛ የክርስትያኖች ህብረት እንደ አካል እያንዳንዳችን ደግሞ እንደ አካል ክፍል ወይም ብልቶች በምሳሌነት ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡
ከአካል ምን እንማራለን?
አካል አንድ ነው
አካል አንድ ነው፡፡ ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል ግን አንድ ነው፡፡ የአካል ብልቶች የተለያዩ መሆናቸው የተለያየ አላማ እንዲኖረንና ለተለያየ መንግስት እንድንሰራ ፈቃድ አይሰጠንም፡፡ ለተለየ መንግስት ከሰራን ለእግዚአበሄር መነግስት ሳይሆን ለራሳችን መንግስት ነው እያሰታን ያለነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ለተለያየ አላማ የመስራት ጥሪ የሌለን፡፡ ሁላችንም የምንሰራው ለአንድ መንግስት ለአንድ ግንብ ነው፡፡
ብልቶች የተለያዩ ናቸው
የብልቶችን ልዩነት መቀበል የአካልን አንድነት እንደመቀበል አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ከእርሱ የተለየ ሰው ሁሉ ስህተት ይመስለዋል፡፡ ሌላው ጃካለእርሱ ሌላው ጌታ የሚሰራበት አይመስለው፡፡ ለዌላው ደግሞ በእርሱ መንገድ ያልገሄድ ነበትክክለፃ መንገድ እንዳልሄደ ይመስለዋል፡፡
የብልቶች ልዩነት ውበት ነው
የብልቶች ውበት በልዩነታቸው ውስጥ ነው፡፡ ብልቶች ካልተለያዩ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም ነገር አንድ አይነት ቢሆን እንዴት ያለ ውድቀት ነው? ሁላችንም አንድ አይነት ከሆንን እንዴት ያለ አሰልቺ ነው፡፡
አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡17
ከእኛ ለተለየ ሰው ልባችንን ልናሰፋ ይገባል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ይጠቅመናል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው የእኛን ጉድለት ይሞላል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው እኛ ማድረግ የማንችለውን መነገር ያደርግልናል፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ውበታችን ነው፡፡
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡12
በሁላችንም የሚሰራ አንድ እግዚአብሄር ነው
የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡4-6
ማንም እንዲህ ላገልግል ብሎ በራሱ የሚያገለግል የለም፡፡ የሚያገለግል ከሆነ እግዚአብሄር ነው በውስጡ ያስቀመጠው እግዚአብሄርም ነው በፀጋው የሚያስታጥቀው፡፡ አንተን እግር ያደረገህ እግዚአብሄር ነው ሌላውን አይን ያደረገው፡፡
የብልቶች ውድድር ሞኝነት ነው
ብልቶች እያንዳንዳቸው የተለየ ጥሪ አላቸው፡፡ የተለያየ ጥሪ ያላቸውን ለማወዳደር እንደማይቻል ሁሉ በብልቶች መካከል ያለ ውድድር ከንቱ ነው፡፡ የሚታገል ሰውንና ሯጭን ማፎካከር እንደማይቻል ሁሉ የተለያየ ጥሪ ያለንን ማወዳደር አይቻልም፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር ለመፎካከር የራሱን ጥሪ ጥሎ ያልተጠራበትን ጥሪ ማድረግ ይኖርበታል ፡፡ ስለዚህ ነው ፉክክር የህይወት ብክነት የሚሆነው፡፡ ሰው ከጎረቤቱ ጋር ከተፎካከረ ስቷል ማለት ነው፡፡
አንዱ አንዱን ይነካዋል
የአንዱ መደከም የሌላው መድከም ነው የአንዱ መጠንከር የሌላው መጠንከር ነው፡፡ አንዱ አንዱን እንዲያሟላው እንጂ እንዱ አንዱን እንዲፎካከረው አልተሰራም፡፡ አንዱ በሌላው ውድቀት ካልታመመ አንዱ በሌላው ስኬት ካልተደሰተ ከአካል ብልትነት ውጭ እየኖረ ነው ማለት ነው፡፡
አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡26
አንዱ አንዱን ይሞላዋል
እጅ ውስጥ የተቀመጠው ችሎታ እና በረከት ለእግር ጥቅም ነው፡፡ የአይን ፀጋ ለጆሮ ያስፈልገዋል፡፡ የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ድካም የታቀደና የተሰራ ነው፡፡ አካል ሙሉ የሚሆነው ሁሉም ብልቶች በትክክል ሲሰሩ ነው፡፡
ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22-23
አንዱ ለሌላው ያስፈልጋል
ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡21
አንዱ ብልት ለሌላው ብልት ይጠቅማል፡፡ የአንዱ ብልት መሳካት በሌላው ብልት መሳካት ላይ የተመሰረት ነው፡፡ አንዱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ያስፈልጋል፡፡ አያስፈልግም የምንለው የአካል ብልት የለም፡፡ ከሚታየው እስከ ማይታየው ከትልቁ እስከ ትንሹ የአካል ብልት ጠቃሚ ነው፡፡ የአለማችን ሳይንቲስቶች ስለአካችን ክፍሎች ጥቅም በክፍለ ዘመናት እየተመራመሩ ይገኛሉ ግን ሁሉንም የአካል ክፍል ጥቅም አውቀው አልጨረሱትም፡፡ እንዲሁም የማይጠቅም የሚመስለን የአካል ብልት ካለ ራሳችንን ትሁት እናድርግ፡፡ ይ-ጠ-ቅ-ማ-ል፡፡
ይህን ሁሉ በስፍራው የሚያስይዘው የእኛ ትህትና ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ልዩነት #አካል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #አንድነት #ፀጋ #ብልት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment