ጥምቀት ወሳኝ የክርስትና ህይወት ክፍል ነው፡፡
እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ማርቆስ 16፡15-16
ኢየሱስን ለመከተል ማስተዋል ስንችልና በራሳችን ስንወስን እንጠመቃለን፡፡
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው እኛን ከሃጢያት እስራት ሊያድን ነው፡፡ ኢየሱስ ሰውን ከሃጢያት የሚያድነው በሞቱና በትንሳአው ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ በመስቀል ላይ ስለሃጢያታችን ሲሰቀል ፣ ሲሞት ፣ ሲቀበርና ሞትን ድል አድርጎ በሶስተኛው ቀን ሲነሳ ያንን ሁሉ የሆነው ስለራሱ ሃጢያት አልነበረም፡፡
ኢየሱስ የሞተውና የተነሳው ስለእኛ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሞተውና የተነሳው እኛን ወክሎ በእኛ ፋንታ ነበር ፡፡
እኛም ኢየሱስን አምነን እንደ አዳኝና ጌታ ስንቀበለው እግዚአብሄር በመለኮታዊ አሰራሩ ከሀጢያት እስራት ነፃ ያወጣናል፡፡
እኛ ኢየሱስን ስንቀበል እንጠመቃለን፡፡ ጥምቀት ከኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ጋር ራሳችንን የማስተባበሪያው መንገድ ነው፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ሲሰቀል እኛን ሃጢያት የሚያሰራንን የሃጢያትን ምኞት ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር በመስቀል ላይ እንደሰቀለው ከስቅለቱ ጋር የምንተባበርበት መንገድ ነው፡፡
ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና።መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል። ሮሜ 6፡9-11
እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ።
በውሃ ጥምቀት ለሃጢያትና ለአለም ክፉ ምኞት ሞቻለሁ ብለን እናውጃለን፡፡ ስንጠመቅ ከሞተውና ከተቀበረው ኢየሱስ ጋር ራሳችንን እያስተባበርን ነው፡፡ ኢየሱስ በመቃብር እንደተቀበረ እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር ለመተባበር በውሃ ስር እንቀበራለን፡፡ በውሃ በመጠመቅና በውሃ ውስጥ በመስመጥ ከመቀበሩ ጋር ራሳችንን እያስተባበርን ነው፡፡
ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? ሮሜ 6፡2-3
ከውሃ ስንወጣ ደግሞ በአዲስ ህይወት ለመመላለስ ከአሁን በኋላ ለጽድቅ ህያው ለመሆን ከኢየሱስ ከሞት ከመነሳቱ ጋር ራሳችንን እናስተባብራለን፡፡
ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤ ሮሜ 6፡5
ጥምቀት ስናስብ ለስጋ ክፉ ምኞትና ለሃጢያትና ለአለም መሞታችንን ትርጉም ካልሰጠን ከንቱ ነው፡፡ ጥምቀትን ስናስብ ከሃጢያት የበላይ የሆነን አዲስ ህይወትን እንዳገኘን በትንሳኤ ለመመላለስ ትርጉም ካልሰጠን ጥቅም የለውም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ጥምቀት #ሞት #ትንሳኤ #መቀበር #አዲስህይወት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment