Popular Posts

Follow by Email

Thursday, January 26, 2017

የዘላለም አምላክ

አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡28
አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሄ ፊት የምናገራቸው ነገሮች እግዚአብሄርን የማያከብሩ አላዋቂነታችንን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሄር በላይ ያወቅን ይመስለናል፡፡ ለእግዚአብሄር ምክር መለገስ የምንችል ይመስለናል፡፡ ስንደክም እግዚአብሄርም አብሮን የሚደክም የቆሎ ጓደኛችን ይመስለናል፡፡ እግዚአብሄር አባታችንም ቢሆን የቆሎ ጓደኛችን ግን አይደለም፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት በጥንቃቄ ልናደርገው ይገባል፡፡ አክብሮት የጎደላቸውና ንግግሮችና ዝንባሌዎች ከህይወታችን ልናስወግድና በትህትና ከእግዚአብሄር ጋር ልንኖር ይገባል፡፡  
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? . . . ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ሚክያስ 6፡8
ልትሰማና ልታውቅ ይገባል ይላል እግዚአብሄር፡፡ የዚህ ሁሉ ንግግር ምንጩ አለማወቅ ነው፡፡
እግዚአብሄ የዘላለም አምላክ ነው
አግዚአብሄር ተለማማጅ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አንተን እንዴት እንደሚመራ ፣ አንተን እንዴት እንደሚይዝህና እንደሚንከባከብህ ፣ አንተን እንዴት እንደሚያስተዳድርህ ከጊዜ ወደጊዜ ልምድን እያካበተ የሚሄድ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም የነበረ መሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘመናት ጀምሮ ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሄር እንዴት ሊይዝህ እንደሚገባው ለመምከር ከዳዳህ እባክህ አፍህን አታበላሽ፡፡ እግዚአብሄርን አትመክረውም፡፡
የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ሮሜ 11፡34-35
እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው
እግዚአብሄር ሃያል ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያለውን የሃይል መጠን ተረድተን አንጨርሰውም፡፡ እግዚአብሄር በምድር ውስጥ እንዳንድ ነገሮችን ያገኘ ሳይንቲስት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር በቀናት የፈጠራቸውን ነገሮች የአለም ምርጥ ሳይንቲስቶች በክፍለ ዘመናት ሁሉ ተማራምረው ተመራምረው ተመራምረው አልጨረሱትም፡፡  
የእግዚአብሄር ማስተዋል አይመረመርም
እግዚአብሄርን ተረድተን ለመጨረስ መሞከር የውድቀት መጀመሪያ ነው፡፡ ማድረግ የምንችለው የተሻለው ነገር በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ማረፍ ብልህነት ነው፡፡ በእግዚአብሄር በጎነት ላይ መደገፍ ጥበብ ነው፡፡ የሚያስጨንቀንን በእርሱ ላይ መጣል የአባት ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርምያስ 29፡11-13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #የዘላለምአምላክ #የምድርዳርቻ #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment