ሰው ሲፈጠር በእግዚአብሄር ክብር ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው ሲፈጠር በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒያት ስልጣኑን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ በመስቀል ላይ በመሞት ለመክፈል ወደ ምድር መጣ፡፡
ኢየሱስ የሞተውና ከሙታን የተነሳው ስለእኔ ሃጢያት ነው ብሎ ኢየሱስን እንደ አዳኙና የህይወቱ ጌታ አድርጎ የሚቀበለውን ማንኛውም ሰው እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ ወደ ቤተሰቡ ይቀበለዋል፡፡ የልጅነት ስልጣኑን ይመልስለታል፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐንስ 1፡12
ግን የእግዚአብሄ ልጅነት ስልጣን ምንድነው?
1. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም የመኖር ስልጣን ነው፡፡
ሃጢያት የሰውን ልጅ ከእግዚአብሄር ተልይቶዋል፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ሞት በመሆኑ ሰው ከእግዚአብሄር ለዘላለም ተለይቶዋል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ በሃጢያት ውጤት በዘላለም ሞት ፍርድ ስር ወድቆዋል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ሰው እግዚአብሄር ስለሚቀበለው ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር የመኖር ስልጣን አለው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንሰ 3፡16
2. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን የእግዚአብሄር መኖሪያ የመሆን ስልጣን ነው፡፡
ኢየሱስን በተቀበለ ሰው ውስጥ እግዚአብሄር ይኖራል፡፡ ኢየሱስን የሚከተለ ሰው መንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16
3. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን የመንፈሱን መያዣ የመቀበያ ስልጣን ነው፡፡
ሰው አንድ እቃ ለመግዛት ፈልጎ ገንዘብ ቢጎድለው እቃውን መግዛት እንደሚፈልግ ማረጋገጫ ቀብድ ይከፍላል፡፡ ቀብድ የከፈለው ሰው እያለ እቃው ለሌላ ሰው አይሸጥም፡፡ ያን ቀብድ የከፈለ ሰው ሌላ ጊዜ መጥቶ የቀረውን ዋጋ ሲከፍል እቃው የእርሱ ይሆናል፡፡
ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡5
እንዲሁንም እኛ የእግዚአብሄር መሆናንችንን ደግሞም በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሄር ጠቅልሎ የራሱ እንደሚያደርገንም ማረጋገጫ መንፈሱን እንደቅድሚያ ክፍያ ቀብድ ሰጭጥቶናል፡፡ የእግዚአብሄ ልጅ የሆነ ሰው የቤተሰቡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስን የመሞላት ስልጣን አለው፡፡
4. ለሚበላና ለሚጠጣ ከመጨነቅ በላይ እንድንኖር ስልጣን ተሰጥቶናል
እግዚአብሄር አባታችን ነው፡፡ አባታችን እግዚአብሄ ከእኛ የሚፈልገው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን እንድንፈልግ ነው፡፡ አህዛብ የሚፈልጉትን እንዳንፈልግ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡ እኛ እንድንፈልግ የታዘዝነው የእግዘኢአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ነው፡፡ ሌላው እንዲጨመርልን ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡
5. በእግዚአብሄር ልጅነታችን በሃጢያት ላይ ስለጣን ተሰጥቶናል
የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን በኋላ ሃጢያት አይገዛንም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የሃጢያተኛ ስጋችንን በመስቀል ላይ ሰቅሎታል፡፡ ስለዚህ አሁን ከሃጢያት ሃይል ነፃ ወጥተናል፡፡ በሃጢያት ላይ ሃይል ተሰጥቶናል፡፡
ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14
6. በሰይጣል ላይ የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን አለን
ኢየሱስ በምድር ላይ ሰይጣንን ድል ነስቶታል፡፡ ኢየሱስ ሰይጣንን ድል የነሳው በእኛ ምትክ ለእኛ ነው፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10፡18-19
7. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ከሁኔታዎች በላይ እንድኖር የሚያስችል ታላቅ ስልጣን ነው፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን ካስቀመጠው አላማ ሊያደናቅፈን በሚመጣ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ ሰዎች 8፡37-39
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #ስልጣን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ሃይል #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment