Popular Posts

Wednesday, January 11, 2017

የሃሳብ ሃይል


በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7
ሃሳብ በሰው ህይወት ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ሰው ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት አስቦ ነው የሚያደርገው፡፡ ሰው ህይወቱ የሚበላሸው ሃሳቡ ሲበላሽ ነው፡፡ የሰው ህይወት መለወጥ የመጀመሪያው እርምጃ የሃሳብ መለወጥ ነው፡፡
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ስለሃሳብ አበክሮ የሚያስተምረው፡፡
ሰው የሚቀደሰውና ከአለም የሚለየው በሃሳብ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ሰው ሃሳቡን የመግራት ስልጣን አለው፡፡
ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። መዝሙር 42፡5
ሰው ስለሚያስበውና ስለማያስበው ነገር ስርአት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሰው ወደአእምሮ የሚመጣውን ነገር ሁሉ ካሳበ ህይወቱ የሰይጣን ሃሳብ ማስተናገጃ ይሆናል፡፡ ሰው የሚያሰበውን ነገር በእነዚህ መመዘኛዎች ሊመዝናቸው ይገባል፡፡ ሃሳቦች ይህንን መመዘኛ ካላሟሉ በፍጥነት ከአእምሮው ሊያስወጣቸው ይገባል፡፡
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ፊልጵስዩስ 4፡8
ሰው ሃሳቡን የሚገራው በእግዚአብሄር ቃል ነው ፡፡ የነፍሳችሁ ክፍል የሆነው አእምሮዋችሁ የሚፈወሰው በእግዘኢአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21
ሰው ህይወቱን የሚያጠራው ሃሳቡን በማጥራት ነው፡፡  
ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። ያዕቆብ 4፡8
ሰው ሃሳቡ ከተበላሸ ህይወቱ ይበላሻል
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡3
የእግዚአብሄርን ቃል ማሰብና ማሰላሰል ቃሉን ለመፈፀምና ለመከናወን ግዴታ ነው፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ 1፡8
ሰው እግዚአብሄርን መፍራት ያለበት ከአስተሳሰቡ ጀምሮ ነው፡፡ በሃሳቡ እግዚአብሄርን የማይፈራና የፈለገውን ለማሰብ ለስጋው አርነት የሚሰጥ ሰው መቼ እንደወደቀ ሳያውቅ ወድቆ ይገኛል፡፡
ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። ዘፍጥረት 3፡6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #አእምሮ #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment