Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, January 25, 2017

በገድል አምናለሁ!

መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
የምንኖረው ጠላት ዲያቢሎስ በሚሰራበት አለም ውስጥ ነው፡፡ ኢየሱስን ለመከተል ስንወስን በቅፅበት የሰይጣን ጠላቶች ሆነናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በምድር የሰጠንን ሃላፊነት ሰርቶ ለማለፍ ተጋድሎ ይጠይቃል፡፡
ይህ የእምነት ተጋድሎ እግዚአብሄ የሰጠን ተጋድሎ ስለሆነ መልካም ተጋድሎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያልሰጠን ተጋድሎዎች በሙሉ መልካም ተጋድሎዎች አይደሉም ውጤትና ፍሬም የላቸውም፡፡ ሰው በራስ አነሳሽነት የሚታገላቸው ተጋድሎዎች ውጤት አልባና የብክነት ተጋድሎዎች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ሰው ከሰው ጋር ያለው ተጋድሎ ፣ ከሰው ጋር ያለ ፉክክርና ከንቱ ውድድር መልካም ያልሆነ ተጋድሎ ነው፡፡ ከሰው ጋር የምናደርገው የጦርና የጠብ ተጋድሎ እግዚአብሄር የሰጠን መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡2-3
ሰው በራሱ መንገድ እግዚአበሄርን ለማስደሰት የሚያደርገው ተጋድሎ መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡ መልካም ተጋድሎ እግዚአብሄር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን አዳኝና ጌታ አድርጎ መቀበል ነው፡፡ ሰው ግንብ ይህንን ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለለትን የሃጢያት እዳ ክፍያ ትቶ በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ለማስደሰት መሞከር መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡  ሰው በግብረገብ ለመዳን መሞከርና መፍጨርጨር ኢየሱስ የከፈለውን መስዋእት ከንቱ ስለሚያደርገው መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡ ሰው በራሱ ህግን ለመፈፀም መሞከር እግዚአብሄር የሚፈልገው ውጤታማ ተጋድሎ አይደለም፡፡ ህግን ጠብቆ ለመዳን መሞከር ከነፃ የእግዚአብሄር ስጦታ ከደህንነት ፀጋ መንገድ መውደቅ ነው፡፡   
በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ገላትያ 5፡4
ስለሚበላና ስለሚጠጣ የምንጨነቀው ጭንቀትና ተጋድሎ እግዚአብሄር ጎሽ የሚለው ተጋድሎ አይደለም፡፡ ሰው አስቀድሞ የእግዚአብሄርን መንግስት መፈለግ ነው ያለበት፡፡ ሰው ግን የእግዚአብሄርን መንግስት ከመፈለግ ይልቅ ስለሚበላና ስለሚጠጣ ላይ ታች ማለቱ መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡  
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ማቴዎስ 6፡31
ይህን ተጋድሎ ልዩ የሚያደርገውና መልካም ያሰኘው እግዚአብሄር ከእኛ የሚጠብቀው ብቸኛ ተጋድሎ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ተጋድሎ እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ብቸኛው ተጋድሎ ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ይህ ተጋድሎ እግዚአብሄር አብሮት የሚሰራ ተጋድሎ ነው፡፡ ይህ ተጋድሎ ብክነት የሌለበት ፍሬያማ ተጋድሎ ነው፡፡ ይህ ተጋድሎ ውጤቱ ሁልጊዜ ድል የሆነ ተጋድሎ ነው፡፡
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4
የእምነት ገድል እግዚአብሄር ቃል ላይ በመቆምና በመፅናት የምንጋደለው ተጋድሎ ነው፡፡ የእምነት ገድል ኢየሱስ በመስቀል ላይ የፈፀመልንን ድል የእኛ ድል አድርገን መኖር ነው፡፡ የእምነት ገድል እግዚአብሄር በምድር ላይ የሰጠንን አላማ እስከመጨረሻው ማስፈፀም ነው፡፡ የእምነት ገድል እግዚአብሄር የሰጠንን አገልግሎት መምድር ላይ ፈጽመን እግዚአብሄን ማስከበር ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ተጋድሎ #አላማ #ቃል #ውጤት #ድል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment