በክርስትና ህይወት የእግዚአብሄርን ነገር መራብና መጠማት ወሳኝ ነው፡፡ ፅድቅን መራብና መጠማት የመንፈሳዊ ጤንነት ምልክት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች ብፁአን ናቸው፡፡
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። ማቴዎስ 5፡6
በክርስትና ህይወታቸው ፅድቅን መራብ ጀምረው ሲቆይ ወደኋላ ያሉ ብዙ ሰዎችን እናውቃል፡፡ በመልካም ጀምረው የፅድቅ ረሃብና ጥማታቸው በመንገድ ላይ የጠፋባቸው አያሌ ሰዎች ታዝበናል፡፡ የጌታን ቃል ሰምተው የማይጠግቡ የነበሩ በኋላ ግን ያንን ወሳኝ ረሃብና ጥማት የጣሉ ሰዎችን ታዝበናል፡፡
ረሃባችንንና ጥማታችንን የማጣት አደጋ በሁላችንም ላይ አለ፡፡ ፍላጎት ማጣት ሁላችንንም ሊፈትንና ሊጥል የሚችል ፈተና ነው፡፡ ዝለን የእግዚአብሄርን ነገር በትጋት ከመፈለግ ዘወር እንድንል እንፈተናለን፡፡
በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። ዕብራውያን 12፡3
ይህንን ወሳኝ በረከት እንድናጣው የሚያደርገን ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ በዚያ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ይረዳናል፡፡
1. ቃሉን በሚዛናዊነት አለመጠበቅ
ለፅድቅ ያለንን ረሃብና ጥማት ሊያጠፋውና ከሩጫችን ሊገታን የሚችለውና ነገር አንድን የእግዚአብሄር ሃሳብ ብቻውን በከፍታ ይዞ ሌላውን መጣል ወይም ማሳነስ ነው፡፡ አንዱን የእግዚአብሄ ቃል ለማጠናከር ሌላውን ማሳነስ የለብንም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ሙሉ ነው፡፡ ሁሉም የእግዚአብሄር ቃል ጠቃሚ ነው፡፡ ሙሉ የእግዚአብሄር ቃል ነው ሙሉ የሚያደርገን፡፡
ሰው ድንችን ብቻ በየእለቱ በመመገብ ጤናማና ብርቱ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲሁም ሰው ያልተመጣጠነና ሚዛኑን ያልጠበቀ ትምህርት በመመገብ ለእግዚአብሄር ነገር ያለውን ጤናማ ፍላጎት ሊያጣው ይችላል፡፡
ለሰው መንፈሳዊ ጤንነት ሙሉ የእግዚአብሄ ምክር አስፈላጊ ነው፡፡ ሰው ፍሬ የሚያፈራው ሙሉውን የእግዚአብሄን ቃል ምክር በመረዳት ብቻ ነው፡፡ ሰው አንዱን ወይም ጥቂት ቃል ብቻ በመያዝና በማጋነን ጤናማ መንፈሳዊ ረሃቡንና ጥማቱን ሊጠብቀው አይችልም፡፡
አንዱ የእግዚአብሄር ቃል ተነጥሎ ብቻውን ስለማይሰራ ሰው አጋኖ በያዘው ቃል ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ቃሉ ይሰራል ሃያልም ነው፡፡ በቃሉ ምንም ችግር የለም፡፡ ሙሉውን ቃል በሚዛናዊነት ካልያዝነው እውነተኛውን መንፈሳዊ ፍላጎት እናጣዋለን፡፡
የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። ሐዋርያት 20፡27
2. ለደረጃችን ከሚመጥነን በላይ የእግዚአብሄን ቃል ለመረዳት መሞከር
ህፃን ምግብ መብላት የሚጀምረው በወተት ነው፡፡ ወተቱ ያጠነክረዋል ለጠንካራ ምግብ ያዘጋጀዋል፡፡ በወተት ላልተፈተነ ህፃን ጠንካራ ምግብ መስጠት አደገኛ ነው፡፡ ህፃንን ካለጊዜው ስጋ ካበላነው ጤንነቱ ይዛባል፡፡ ለወተት ያለው ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ይቀንሳል፡፡
እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች በፍጥነት ማደግ ይጓጓሉ፡፡ መሰረታዊ የክርስትና ትምህርት ከመማራቸው በፊት ጠንካራ ምግብ ለመብላት ሲሞክሩ ጤንነታቸው ይዛባል፡፡ በፍጥነት ማደግ ከመፈለጋቸው የተነሳ የእግዚአብሄርን የማሳደግ ሂደት አይታገሱም፡፡
ቃሉን በአእምሮዋቸው ስለሚያቁት ብቻ የደረሱበት ይመስላቸዋል፡፡ ሰው ግን ደረሰበት የሚባለው በህይወቱ ሲተገብረው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አዳዲስ መገለጦች ለማግኘት እንደመፈለጋችን በምናውቀው ቃል ለመኖር ራሳችንን ማስለመድ ይገባናል፡፡
ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ያዕቆብ 1፡22
እነዚህ አይነት ሰዎች ሁሉንም ባንድ ጊዜ አውቀው ለመጨረስ ያላቸው ፍላጎት ስለማይሟላ ይሰናከላሉ ለመንፈሳዊ ነገር ያላቸው ፍላጎት ይጎዳል፡፡
3. በቀዳሚነት ከእግዚአብሄር ቃል መፍትሄን አለመፈለግ
ህፃናት ልጆች ሰውነታቸውን ስለሚጠቅማቸውና ስለማይጠቅማቸው መረዳቱ ስለሌላቸው በምግብ ወላጆችን ያስቸግራሉ፡፡ ህፃን ከረሜላ ካገኘ ጣፋጭ ስለሆነ ብቻ የቻለውን ያህል መምጠጥ ይፈልጋል፡፡ ከረሜላው ጣፋጭ ነው እንጂ ያለው የምግብ ይዘት በጣም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ህፃኑ ያንን ከረሜላ እንደበላ የምግብ ፍላጎቱ ይዘጋል፡፡ ስለዚህ ህፃኑ የሚጠቅመውን ተመጣጣኝ ምግብ መብላት አይችልም፡፡ ህፃኑ ጥቅሙ ጥቂት በሆነ ጣፋጭ ነገር የምግብ ፍላጎቱ በመዘጋቱ ለሰውነቱ የሚጠቅመውን የተመጣጣነ ምግብ ሳያገኝ ይቀራል፡፡
እንደዚሁ በክርስትና የእግዚአብሄርን ቃል አንበብን ተረድተን ታዘነው በህይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ በቃሉ ከመፅናትና ከመታገስ ይልቅ ፈጣን መፍትሄን ለመፈለግ እንፈተናለን፡፡ ስላለንበት ሁኔታ እግዚአብሄር በፈጣን ምልክቶችን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ይጠቀምባቸዋል ብለን ወደምናስባቸው ሰዎች በመሄድ እግዚአብሄ ስለእኔ ምን ይልሃል ብለን ለመጠየቅ እንፈተናለን፡፡ እውነተኛንና ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት በቀዳሚነት በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ መፍትሄን መፈለግ ይገባናል፡፡
በቀዳሚነት መፍርትሄ መፈለግ ያለብን ከቃሉ ውስጥ ስለሆነ በራሳችን መፀለይና እግዚአብሄር እንዲናገረን ጊዜ መስጠት አለብን፡፡ ለመፍትሄ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ያለን ትኩረት ሲነሳ ህይወታችን ለብዙ ነገር ይጋለጣል፡፡
በዚህም ምክኒያት ላለንበት ሁኔታ በቀዳሚነት ከትንቢት አገልግሎት መፍትሄን ለማግኘት እንፈልጋለን፡፡ የጠበቅነው ነገር ሳይሆን ሲቀር የትንቢት አገልግሎት አይሰራም ብሎም የእግዚአብሄር ነገር አይሰራም ወደማለት እንሄዳለን፡፡
በዚያም ሁሉንም የእግዚአብሄርን ነገር እርግፍ አድርገን ለመተው እንፈተናለን፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ነቢያትም አሉ እግዚአብሄርም በዚህ ዘመን በትንቢት ይሰራል ነገር ግን እግዚአብሄር ለልባችን በቀዳሚነት ከሚናገረን ይልቅ እግዚአብሄር በቀዳሚነት በትንቢት እንደሚናገር ከጠበቅን ስለማይሰራልን ለእግዚአብሄ ነገር ያለንን ፍላጎት ረሃብና ጥማት ይጎዳዋል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መጠማት #መራብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment