Popular Posts

Monday, December 2, 2019

ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም



ከአለቆችም አንዱ፦ ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። የማርቆስ ወንጌል 10፡18-19
ኢየሱስ የእኛን አይነት ስጋ ለብሶ ሰው ሆኖ በምድር በተመላለሰበት ጊዜ ቸር መምህር ሆይ ተብሎ እንዲጠራ አልፈቀደም፡፡ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ሲመላለስ ለተጠየቀው ጥያቄ የመለሰው መልስ በጣም አስገራሚ ነው፡፡
ኢየሱስ እንኳን በምድር ሲመላለስ ቸር ተብሎ እንዲጠራና የእግዚአብሔር አብን ክብር ለመውሰድ አልፈቀደም፡፡ ምክኒያቱም በሰው ውስጥ መልካምነት አይገኝም፡፡ ሰው መልካምነት ካሳየ ከእግዚአብሔር የመጣ መልካምነት መሆን አለበት፡፡ የመልካም ሰውን መልካምነት አመጣጥ ለማወቅ ተከትልን ብንሔድ የምንደርሰው ራሱ እግዚአብሔር ጋር ነው፡፡
በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። የያዕቆብ መልእክት 1፡17
የማንም ሰው መልካምነት ወደምንጩ ወደ እግዚአብሔር ካላመለከተ መልካምነት አይደለም፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ  ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የማንም ሰው መልካምነት ማመልከት ያለበት ወደ ምንጩ ወደ እግዚአብሔር መሆኑን ለማስተማር ነው፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። የማቴዎስ ወንጌል 5፡16
ሰው መልካም ሊያደርግላችሁ አስቦ አቅዶ በራሱ ጉልበት መልካም ሊያደርግላችሁ አይችልም፡፡ ሰው አብሯችሁ ሊቸገር ይችላል ነገር ግን በራሱ መልካምን ሊያደርግላችሁ ግን አይችልም፡፡
ሰው እግዚአብሔር ካልረዳው አቅዶና አስቦ ለራሱ እንኳን መልካም ሊያደርግ አይችልም፡፡
አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሔዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። የያዕቆብ መልእክት 4፡13
ሰው እግዚአብሔር ካልተጠቀመበት ምንም መልካም ነገር ሊያደርግላችሁ አይችልም፡፡ ሰው ምንም መልካም ነገር ካደረገላችሁ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ነው መዝሙረኛው ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም የሚለው፡፡  
እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። መዝሙረ ዳዊት 16፡2
እግዚአብሔር ካልተጠቀመብን ለምንም አንጠቅምም፡፡ እግዚአብሔር ከተጠቀመብን ደግሞ የማንጠቅመው ነገር አይኖርም፡፡ እግዚአብሔ ካልተጠቀመብን ለጥቂትም አንጠቅምም፡፡ እግዚአብሔር ከተጠቀመብን ደግሞ በብዙ እንጠቅማለን፡፡  
ከሰው መልካምነት ባሻገር ማየት የመልካምነቱን ምንጭ እግዚአብሔርን ራሱ ማየት ካልቻልን እንሳሳታለን፡፡ ለሰው በቀጥታ መልካምነትን የሚያደርገው ሰው ነው፡፡ ለሰው በተዘዋዋሪ መልካምነትን የሚያደርገው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡  
ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። የማርቆስ ወንጌል 10፡18-19
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #አመስግኑ #መልካም #ቸር #ደግ #በጎ #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ቸር #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

No comments:

Post a Comment