Popular Posts

Tuesday, December 3, 2019

የእግዚአብሔር አላማ የሌለበት ሀገር

እግዚአብሄር የአላማ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን በግብታዊነት ሳይሆን በአላማ ነው፡፡ እግዙአብሄር የፈጠረን አላማውን የምንፈፅመብት አገር ላይ ነው፡፡ የምንኖርበትን አገር የወሰነው እግዚአብሄር ነው፡፡
ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። የሐዋርያት ሥራ 17፡26-27
እግዚአብሄር ያስቀመጠንን አገር መለወጥ ያለብን እግዚአብሄር ሲመራን በእግዚአብሄር ፈቃድና በእግዚአብሄር ጊዜ ብቻ መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሄር ካልመራን በስተቀር ያለንበት አገር ላይ እንደመኖር አስተማመኝ ቦታ የለም፡፡ እግዚአብሄር እኛን ለመድረስ እና ለመባረክ ቦታ አይወስነውም፡፡ እግዚአብሄርን ታዝዘን በሰው አይን ድርቅ በሆነበት ቦታ እግዚአብሄር ህይወታችንን ሊያለመልመው ለብዙዎች መነሳት ምክኒያት ሊያደርገን ይችላል፡፡
በምድርም ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ራብ በላይ ራብ ሆነ፤ ይስሐቅም ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ እግዚአብሔርም ባረከው። ኦሪት ዘፍጥረት 26፡1፣2፣12
ለምንሰራው ስራ ብቻ ሳይሆን ለምንሰራበት ቦታ እና አገር ጌታ ግድ ይለዋል፡፡ እግዚአብሄር ስለዝርዝር ህይወታችን ግድ ይለዋል፡፡
እንኳን አገርን ይቅርና ስለምንኖርበት ሰፈር እግዚአብሄር ግድ ይለዋል፡፡ ስለዚህ አገራችንን ከመልቀቃችን በፊት በምንሄድበት አገር ላይ የእግዚአብሄር አላማ እንዳለ ማረጋገጥ አለብን፡፡
እግዚአብሄር አብሮን እንደሚወጣ ካላረጋገጥን በስተቀር መልካም ነገር ለማግኘት ብለን ብቻ አገራችንን መቀየር የለብንም፡፡ ልዩነት የሚያመጣው አገሩ ሳይሆን እግዚአብሄር ከእኛ ጋር መውጣቱ ነው፡፡
እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። ኦሪት ዘጸአት 33፡15
እግዚአብሄርን በመፍራትና በመታዘዝ የእግዚአብሄርን አብሮነት ካገኘን ያነሰው ነገር ይሻለናል፡፡
እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል። መጽሐፈ ምሳሌ 15፡16-17
ከሰማይ በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር የእግዚአብሄር አላማ ብቻ ነው፡፡ በሰው አይን ዝቅ ያለ ነገር ግን የእግዚአብሄርን አላማ የምንፈፅምበት ቦታ ለእኛ ገነታችን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን አላማ የማንፈጽምበት ቦታ ምኑም ቢመች ምንም አይጠቅመንም፡፡ የእግዚአብሄር አላማ የሌለበት አገር ልፋት እና መቅበዝበዝ ነው፡፡ የእግዚአብሄር አላማ የሌለበት አገር መንከራተት ነው፡፡
የእግዚአብሄር አላማ ያለበት ቦታ ደግሞ ምንም ከፍታና ዝቅታ ቢሆን የእግዚአብሄር እጅና አብሮነት ስላለበት ብቻ ሁሌ ተመራጭ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተስፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment