Popular Posts

Friday, December 6, 2019

የዝነኝነት ወጪ



ዝነኝነት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እግዚአብሄር ዝነኛ እንድንሆን ከፈለገ ለዝነኝነት የምንከፍለው ዋጋ በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ዝነኝነታችን ለህይወት አላማችን የሚያስፈልግ ከሆነ ለዝነኝነት የምንከፍለው ዋጋ ወጭው በእግዚአብሄር ዘንድ የተሸፈነ ነው፡፡ እግዚአብሄር በውስጣችን ያስቀመጠውን ስጦታ ብዙዎች እንዲጠቀሙ ሲፈልግ እግዚአብሄር ዝናችንን ያወጣዋል፡፡   
እኛ ግን በራሳችን አነሳሽነት ካለን እውቅና በላይ እውቅና ለማግኘት የምንሞክረው ማንኛውም ሙከራ አደገኛ ነው፡፡ እግዘኢአብሄር ከሰጠን የህይወት አላማ በተጨማሪ ዝነኛ ለመሆን የምንሮጠው ሩጫ ከህይወት አላማችን ያዘገየናል ሊያሰናክለንም ይችላል፡፡
በህይወታችን የእግዚአብሄርን አላማ መፈፀም በራሱ ሙሉ ሃሳባችንን ጉልበታችንን ትኩረታችንን የሚጠይቅ ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ከሰጠው የህይወት አላማ በተጨማሪ ዝነኛ የመሆን አላማን ከጨመረበት ህይወቱ ይወሳሰባል፡፡
እግዚአብሄር ሌሎችን እንድናገለግል የሰጠንን ነገር ራስን በማስተዋወቅ ላይ ማዋል ጥበብ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከሰጠን ተሰሚነት በላይ በራስ ዝነኛ ለመሆን መጣር አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ነገር ሁሉ መዋል ያለበት እግዚአብሄር ወደእኛ ያመጣቸውን ሰዎችን በማገልገል እና በመጥቀም ላይ ብቻ ነው፡፡ 
እግዚአብሄር አገልግሎታችንን ሊያሰፋ ብዙዎች እንዲጠቀሙ ሲፈልግ እራሱ እግዚአብሄር ይበልጥ ዝነኛ ያደርገናል፡፡ እግዚአብሄር ዝነኛ ሲያደርግ ካለምንም ማስታወቂያ እንዲሁ መወደድን እና መፈለግን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር ዝነኛ ሲያደርግ እንደበቅ ብንልም አንችልም፡፡ እግዚአብሄር ለአላማው ዝናችንን ሲያወጣው ሞገስ ከተደበቅነበት ቦታ ፈልጎ ያወጣናል፡፡
ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፤ ፈለጉትም፥ አላገኙትምም። ከእግዚአብሔርም፦ ገና ወደዚህ የሚመጣ ሰው አለን? ብለው ደግሞ ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም፦ እነሆ፥ በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል ብሎ መለሰ። እነርሱም ሮጠው ከዚያ አመጡት፤ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 10፡21-23
በተለይ ሰው በራሱ አነሳሽነት ዝነኛ ከሆነ እጅግ ብዙ ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡ ሰው እጅግ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ላለመክፈል በራስ ጥረት የሚመጣ የዝነኝትን ፈተና ማለፍ አለበት፡፡
ኢየሱስ በምድር በሚመላስበት ጊዜ ከጊዜው በፊት የነበረውን ዝነኝነት ይሸሸው ነበር፡፡ ከዝና ጋር አብሮ የሚመጣ ፈተና ስላለ ኢየሱስ ከፈወሰ በኋላ እንኳን የሚያዘው ለማንም እንዳትናገሩ ብሎ ነበር፡፡ 
ኢየሱስም፦ ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው። የማቴዎስ ወንጌል 8፡4
ኢየሱስ ከጊዜ በፊት ያለን ዝነኝነት ይሸሸው ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜው አገልግሎቱ ለብዙዎች መትረፍ ስለነበረበት ዝናው ይወጣ ነበር፡፡ አገልግሎቱ ለብዙዎች እንዲደርስ እግዚአብሄር ስለፈለገ ሰዎች አትናገሩ በተባሉ መጠን አብዝተው ይናገሩ ነበር፡፡ ኢየሱስ ዝነኛ ለመሆን ሳይጥርና ራሱን ሳያስተዋውቅ በጊዜው ዝነኛ እንዳይሆን ያገደው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ 
እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን፦ ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው። ወሬው ግን አብዝቶ ወጣ፥ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር፤ የሉቃስ ወንጌል 5፡14-15
ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። የማርቆስ ወንጌል 7፡36
እግዚአብሄር ብዙዎች በመፈወስ ሊጠቀምበት ጊዜው ሲደርስ ግን የኢየሱስ ዝና ከእስራኤል አልፎ በሶሪያ ሁሉ ወጣ፡፡
ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። የማቴዎስ ወንጌል 4፡24
እኛም ራሳችንን ካለጊዜው ለማስተዋወቅ ከምንጥር እና እግዚአብሄር የሰጠንን ስጦታና ጊዜ በከንቱ ራሳችንን በማስተዋወቅ ላይ ከማባክነው እግዚአብሄር በሰጠን አገልግሎት ላይ ብቻ እናተኩር፡፡ 
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ወንጌል #አላማ #እቅድ #ግብ  #ቃል #ዝራ #የምድርጨው #ስም #ዝና #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment