ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር ለልዩ አላማ ፈጥሮናል፡፡ አንዳችን ከሌላችን የተለየ ጥሪ አለን፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ጥሪ መፈፀም የህይወት ምድብ ስራችንና ተልእኳችን ነው፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠው ሃይልና ፀጋ ለዚህ እግዚአብሄ ለጠራን ተልእኮ የሚበቃ ነው፡፡ ከዚህ ተልእኮ የሚተርፍና የሚባክን ምንም ተጨማሪ ሃይል የለንም፡፡
ከዚህ አንፃር እያንዳንዳችን እግዚአብሄር በውስጣችን ያስቀመጠውን ጥሪ መከተል እንጂ ከእኛ እጅግ የተለየ ጥሪ ካለው ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር አይገባንም፡፡ ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር ጥሪያችንን እንድንጥልና ፍሬ ቢስ እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ከእኛ እጅግ የተለየ ጥሪ ካለው ከሌላው ሰው ጋር በመፎካከር እግዚአብሄር ከሰጠን ጥሪ ወደሃላ የሚጎትቱትን ነገሮች ፀንተን ልንቃወማቸው ይገባል፡፡
የአለምን አሰራር ተከትለን በኑሮ ትምህክት ወሰጥ እንድነጋባ የሚፈትኑትን ነገሮች ተቃቁመንና ከከንቱ ፉክክር ራሳችብን በፈቃዳችንም ራሳችንን አግልለን የተሰጠንን ሩጫ በትግስት እንሩጥ፡፡
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
በፈቃዳችን ራሳችንን ማግለል ያለብን የዘመናችን የፉክክር መድረኮች
1. በምንበላውና በምንጠጣው መመካት
ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ከፍ ላለ ጥሪ ተፈጥሯል፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የማይኖር ሰው በመብላትና በመጠጣት ከመመካት ውጭ ሌላ የተሻለ ነገር ሊያደረግ አይችልም፡፡ ለእኛ የክርስቶስ ተከታዮች ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እኛ የምንበላው እና የምንጠጣው ለመብለጥ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ለማስፈፀም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማገልገል በምንበላበትና በምንጠጣበት አራት ኮከብ ሆቴል አንፎካከርም፡፡
መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡13
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንሰ 6፡27
2. በምንለብሰው አንፎካከርም
ልብስ ሰውነትን ከመሸፈን ባለፈ በአለም ላይ ከፍተኛ የመፎካከሪያ መድረክ ነው፡፡ እከሌ የለበበሰወ ልብስ እንደዚህ አይነት ምልክት ነው፡፡ እከሌ ካለእንደዚህ አይነት ምርት ልብስ አይለብስም፡፡ እከሊት ቀሚስዋን የገዛችው በእንደዚህ አይነት ብር ነው በማለት ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ለመልበስ ይፎካከራሉ፡፡ ይህ ለክርስቲያን እጅግ ያነሰና የማይገባ ፉክክር በመሆኑ ክርስትያን ከዚህ የልብስ የውድድር መድረክ በፍጥነት ራሱን ማግለል አለበት፡፡ እኛን ሊያለብሰብንና ከዚህ እግዚአብሄር ካለበሰን የሞገስ መጠን በላይ ሊያሳምረን የሚችል ብራንድ የለም፡፡
እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? ማቴዎስ 6፡30
3. በሚነዳው መኪና ውድነት መፎካከር
አለማዊያን ከቁሳቁስ ከፍ ያለ የሚወዳደሩበትር ነገር ስለሌላቸው በሚነዱት መኪና ይፎካከራሉ፡፡ በሚነዳው መኪና አይነትና ሞዴል ከማይመለከታቸው ሰዎች ጋር መፎካከር ለክርስቲያን የሚገባ አይደለም፡፡ የመኪና ጥቅም ሰውን ከ ሀ ወደ ለ ማድረስ ነው፡፡ እውነት ነው ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋው ሰዎች ተጨማሪ ምቾት ያለው መኪና ያስፈልጋቸዋል፡፡ የመኪናው ሞዴል ግን በመኪናው ተንቀሳቅሰን ከምንሰራ የእግዚአብሄር የአገልግሎት ጥሪ ይበልጥ መግነን የለበትም፡፡ ሰው ስለሚነዳው መኪና ከሌላው ጋር ከተፎካከረ በኑሮ ትህምክት ወጥመድ ውስጥ ወድቋል ማለት ነው፡፡
4. ስለሚይዘው ስልክ ውድነትና ጥራት
መሰረታዊው የስልክ ጥቅም ሰውን ከሰው ጋር በድምፅ ማገናኘት መሆኑ አንዳንዴ ይረሳል፡፡ ስለዚህ ሰው ውድ ያልሆነ ስልክ ስለያዘ ተደብቆ ስልኩን የሚያነሳው ከሆነ በማይገባው የህይወት ፉክክር ውስጥ ወድቋል ማለት ነው፡፡ ሰው ውድ ባልሆነ ስልክ ከተዋረደ በውድ ስልክ ይመካል ማለት ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ከሚይዘው ስልክ 75 እጁን ቴክኖሎጂ እንደማይጠቀምበት የእያንዳንዳችን የዘወትር እይታ ምስክር ነው፡፡ ብዙ ሰው ከሰው እንዳላንስ ብሎ በሚገዛው ውድ ስልክ ውድ ያልሆነ ስልክ ከሚያደርግለት ነገር በላይ አይጠቀምበትም፡፡ እውነት የምትጠቀምበት ከሆነ ደግሞ ውድ ስልክ ያስፈልግሃል እግዚአብሄርም ይሰጥሃል፡፡
5. የመኖሪያ ቤት ውድነት ወይም አካባቢ
የሚኖርበት አካባቢ ለፉክክር የማይበቃ ስለሆነ አንገቱን አቀርቅሮ የሚገባና የሚወጣ ሰው ውድ ቦታ ቢኖር እንደማየመካ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ መኖሪያ ቤት ከመኖሪያ ቤትነት ባለፈ የሰው ልክ የሚለካበት ከሆነ አደጋ ነው፡፡ ልካችን የሚለካው በእግዚአብሄር ልጅነት ስለሆነ በዚህ በዘቀጠ የፉክክረ መድረክ ላይ በመገኘት በማይመጥነን ተራ ነገር ራሳችንን አናዋርድም፡፡
6. ስምና ዝና
ከእግዚአብሄር ልጅነት በላይ ስልጣን የለም ፡፡ ከንጉስ የቤተሰብ አባልነት በላይ ዝና የለም፡፡ እግዚአብሄር በላያችን ያስቀመጠው ዝናና ስልጣን ለጥሪያችን በቂ ነው፡፡ ጥሪያችንን ለመከተል በተሰጠን ጉልበት ዝናን በማግኘት ሩጫ ላይ አናባክነውም፡፡ ከዚህ በላይ ዝነኛ ለመሆን ከማንም ጋር መፎካከር ለእግዚአብሄር አገልጋይነታችን ክብር አይመጥንም፡፡
7. በልጆች ትምህርት ቤት
እኔ ልጆቼን የማስተምረው በወር ይህ ያህል እየከፈልኩ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ይህን ያህል እከፍላለሁ፡፡ የእኔ ልጆች ትምህርት ቤት እንዲህ ነው እንዲያ ነው በማለት ሰዎች በልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ውድነት ይመካሉ፡፡
በእግዚአብሄር ከመመካት ውጭ ያለውን ትምክት እግዚአብሄር አይቀበለውም፡፡ በመክፈል ችሎታችን በተመካን ቁጥር ደግሞ እግዚአብሄር ልጆቻችንን እንዲባርክ ፣ ልባቸውን እንዲከፍትና እግዚአብሄር በወደፊታቸውና በተስፋቸው እንዲባርካቸው ጌታን ተስፋ ማድርግ ያቅተናል፡፡ ከጎረቤታችን ጋር በልጅ ትምህርት ቤት ፉክክረ ውስጥ ሳንገባ ፣ ሳንጨነቅ መክፈል የምንችለውን በአቅማችን እየከፈልን ስለ ልጆቻችን ወደፊት በእግዚአብሄርት መታመን ይገባናል፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
ስምንተኛውን በመጨመር ለፅሁፉ አስተዋፅኦ ያድርጉ፡፡
በህይወታችን እግዚአብሄር ያስቀመጠውን አላማ ለመፈፀም መብዛት አይጠይቅም፡፡ በምድር ላይ የተፈጠርንበትን የህይወት አላማ ላለመፈፀም ደግሞ መዋረድ አያግደንም፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ አገልገለን ለማለፍ የሚያስፈልገን የእግዚአብሄር ሃይል ብቻ ነው፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ትምክት #ነፃነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አርነት #ፉክክር #ውድድር #ጥሪ #አላማ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ