Popular Posts

Tuesday, November 1, 2016

የፍቅር እውነተኛ ትርጉም

በሰው ህይወት ውስጥ ግንኙነት እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ግንኙነት በትክክል እንዲሰራ የሚያስችለው ነዳጁ ፍቅር ነው፡፡
ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነገር ቢሆንም ስለፍቅር ብዙ የተባለና የተፃፈ ቢሆንም እንኳን እንደ ፍቅር የተደናገረ የተወናበደ ሃሳብ በአለም ላይ አይገኝም፡፡
ፍቅር ምን እንደሆነ ከማየታችን በፊት ፍቅር ምን እንዳልሆነ ማየታችን የሃሳብ እንድነት እንዲኖረን ያስችለናል፡፡
ፍቅር ስጋዊ ፍላጎት አይደለም፡፡ ለአንዳንዶች ፍቅር ማለት ድንገት መጥቶ የሚይዛቸው የማይቆጣጠሩት ስሜት ነው፡፡ ፍቅር ለሌሎች ይጠቅመኛል ለኔ ጥሩ ነው ብለው ወደሚመኙት መሳብ ነው፡፡ ፍቅር ለራስ ወዳድነት ስሜታችን የሚስማማን ነገር ማድረግ አይደለም፡፡ ፍቅር ምኞታችንን መከተል አይደለም፡፡ ፍቅር በህይወታችን ያለውን ጉድለት እጦት የምናሟላበት አቋራጭ መንገድ አይደለም፡፡ ፍቅር ከሌላው የምንወስድበትና ሌላውን ለራሳችን ጥቅም የምንጠቀምበት መንገድ አይደለም፡፡
የፍቅር ትርጉሙ እጅግ የተወናበደ በመሆኑ ብዙ ጊዜ የፍቅር ትርጉሙ ከራስ ወዳድነት ጋር አንድ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ፍቅር ግን ሲጀመር ሰውን መረዳት ነው፡፡ የፍቅር አላማ ስለምንወደው ሰው እንጂ ስለእኛ አይደለም፡፡ ፍቅር የሚያማክለው የምንወደውን ሰው እንጂ የራሳችንን ጥቅም አይደለም፡፡ ፍቅር የእኛ ፍላጎት ሳይሆን የምንወደው ሰው ፍጎትን በማሟላት ላይ ያተኩራል፡፡
ስለዚህ ፍቅር የሚጀምረው የምንወደውን ሰው ፍላጎት በማጥናት ነው፡፡ የምንወደውን ሰው በሚገባ ለመንከባከብ ማጥናት ማወቅ ይጠይቃል፡፡ የምንወደውን ሰው ለማገልገልና ለመጥቀም ማወቅ ይጠይቃል፡፡
እግዚአብሄርን እንወደዋለን እርሱን የሚያስደስተውን ነገር ብቻ ለማድረግ ስለምንፈልግ ቃሉን እናጠናለን፡፡ ሰዎች ስለ እግዚአብሄር ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ ሰዎች ስለ እግዚአብሄ ባህሪ ሲፅፉ እናነባለን፡፡ ምክኒያቱም ከምንወደው ከእግዚአብሄርን ጋር ያለንን ግንኙነታችንን በሚገባ ለመያዝ እግዚአብሄርን ማወቅና መረዳት ስለሚጠይቅ ነው፡፡
እንዲሁምየምንወደው ሰው በሚገባ ለመያዝ ማወቅ ይገባል፡፡ የምንወደውን ሰው ላለማስቆጣት ማጥናት ግድ ይላል፡፡ የምንወደውን ሰው ላለማሳዘን ማወቅ ይጠይቃል፡፡ ከምንወደው ሰው ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሳካ የሚያደርገው ከዚያ ሰው ጋር በፍቅር ለመኖር ስናጠናውና ስናውቀው ብቻ ነው፡፡
የምንወደውን ሰው የምናውቀው የምንረዳውና በትጋት የምናጠናው ራሳችንን ከእርሱ ጋር ለማስተባበር ነው፡፡ ራስን ማስተባበር ማለት የእኛ አድርገን መውሰድ ማለት ነው፡፡ ስለምንወደው ሰው ሃላፊነት እንወስዳለን፡፡ ከምንወደው ሰው ጋር ለመቆጠር እንፈቅዳለን፡፡ የምንወደውን ሰው ድካም የራሳችን ድካም አድርገን እንወስዳለን፡፡ የምንወደውን ሰው ድካም ለመሸፈን ተግተን እንሰራለን፡፡ የምንወደውን ሰው ተግዳሮት የራሳችን ተግዳሮት አድርገን እንወስዳለን፡፡ የምወደውን ሰው በምንችለው ሁሉ እናገለግላለን፡፡ የምንወደው ሰው ህይወት ላይ ዋጋን እንጨምራለን፡፡ የምንወደውን ሰው እንደራሳችን እንይዘዋለን፡፡
ፍቅር ለምንወደው ሰው ስኬት መስራትና ለምንወደው ሰው መነሳት መትጋት ነው፡፡ የምንወደውን ሰው በመረዳት ለምንወደው መልካም ማሰብ ፣ መልካም መናገርና መልካም ማድረግ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ከምንወደው ሰው ጋር ራሳችንን ማስተባበር ነው፡፡
በአጠቃላይ እውነተኛው የፍቅር ትርጉም ከምንወደው ሰው ጋር በመረዳት ራሳችንን ማስተባበር ነው፡፡ Love is identifying ourselves with the person we love in understanding
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትዕግስት #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ

1 comment:

  1. Hi. Sir.. You really are a genius, I feel blessed to be a regular reader of such a blog Thanks so much.. -online kaj💕💋 font copy and paste what is love?

    ReplyDelete