Popular Posts

Follow by Email

Sunday, November 20, 2016

ማን ጠራህ?

ለእግዚአብሄር መንግስት ስራ ተጠርተናል፡፡ ለእዚአብሄር ክብር ተጠጨርተናል፡፡ ጌታን የጌታን ህዝብ ለማገልገል ተጠርተናል፡፡ ለምን እንደተጠራን ማወቅ ለምን እንዳልተጠራን እንድናውቅ ያስችለናል፡፡ ለምን እንዳልተጠራን ካላወቅን እግዚአብሄር ለጥሪያችንን የሰጠንን ጉልበት ጊዜና ገንዘብ ሁሉ በተሳሳተ ቦታ ላይ አላግባብ እናባክነዋለን፡፡ ለምን እንዳልተጠራን ማወቅ ለምን እንደተጠራን ግልፅ እንዲሆንልንና ህይወታችንን በጥበብ እንድንመራ ያስችለናል፡፡
ለምን እንዳልተጠራን እንመልከት
  • · ከሌላው ጋር ለመወዳደር አልተጠራንም
ከሌላው ጋር ተወዳድርህ ያደረግከው ነገር ሁሉ ብክነት ነው፡፡ አንድ እንድትወዳደረው የተሰጠህ ደረጃ እግዚአብሄር የሰጠህ ራእይና ስራ ነው፡፡ የተሰጠህና ያለህ ለዚያ የሚበቃ ጉልበትና ፀጋ ብቻ ነው፡፡ ለሌላ ውድድር የሚበቃ ትርፍ ጊዜ ስለሌለህ ለውድድር የምታወጣው ወጪ ለራእይህ የተሰጠህን ወጪ ቀንሰህ ነው፡፡ በፉክክር የምታጠፋው ጉልበት የራስህን ጥሪ በሚገባ እንዳትፈፅመው ያግድሃል፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ገላትያ 6፡4-5
  • · ለሃሜት አልተጠራንም
ሰው የተጠራው ወንድሙን ሊደግፍና ሊያቀናው ነው፡፡ ወንድሙን በሆነ ባልሆነው የሚኮንን ሰው ህይወቱን እያባከነ ነው፡፡ አንተ ህጉን መጠበቅ ህጉን እንዲጠብቅ ወንድምህን መርዳት እንጂ ወንድምን ማማት ከጉዳት ውጭ ምንም እንደማይጠቅምና ወንድምን ማማት ህጉን ራሱን ማማት እንደሆነ ያስተምራል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ መልእክት 4፡11
  • · ሰውን ለማሰናከል አልተጠራንም
በማንም ሰው ላይ የችግር ምክኒያት እንድንሆን አልተጠራንም፡፡ ሰውን ከመባረክና ከመጥቀም ውጭ ክርስትናን በማንም ላይ ከባድ እንድናደርግ አልተጠራንም፡፡ የሰውን ሸክም ለመሸከምና ሌላውን ለመባረክ እንጂ ማንንም ለማሰናከልና ለማሳዘን አልተጠራንም፡፡
ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር።ሉቃስ 17፡2
  • · ለቅናት አልተጠራንም
እንደ ልጅ እያንዳንዳችን ድርሻ አለን፡፡ እንደጥሪውና እንደተሰጠው ሃላፊነት የአንዱ ድርሻ ከሌላው ድርሻ ይለያል፡፡ የአንዱ የህይወት ተግዳሮት ከሌላው እንደሚለይ ሁሉ የአንዱ ድርሻ ከሌላው ድርሻ ይለያያል፡፡ የአንዱ አቅራቦት ከሌላው አቅርቦት ጥሪው እንደሚጠይቀው ፍላጎት መጠን ይለያያል፡፡ ለጎረቤቴ ያልሰጠውን ስጦታ ከሰጠኝ ጎረቤቴ ያ ስጦታ የሚጠይቀው ተግዳሮት የለበትም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ለጎረቤቴን የሰጠውን ካልሰጠኝ እግዚአብሄር ይመስገን የጎረቤቴ ተግዳሮት የለብኝም ማለት ነው፡፡
ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡16
  • · ለመለያየት አልተጠራንም
ለመለያየት ከፈለግን የሚያለያዩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ትልቁ ነገር መለያየት ሳይሆን ትሁት ሆኖ በአንድ ሃሳብ መስማማትና አንዳችን ለአንዳችን መገዛት ነው፡፡ በትግስት ተቻችሎ ለአንድ አላማ መስራት እንጂ መለያየት ብዙ ጥረት አይጠይቅም፡፡ ትልቁ ነገር አብሮ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ለአንድ አላማ መስራት ነው፡፡
በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ፊልጵስዩስ 2፡1-2
  • · ለማጉረምረም አልተጠራንም
እግዚአብሄር በግሉ የሚንከናከበው እንደኛ አይነት ህዝብ የለም፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ የሚያውቅ ፍፃሜና ተስፋ ያለው ሃሳብ ያለው እንደእኛ ማመስገንና ደስተኛ መሆን ያለበት ሰው የለም፡፡ ሁሉንም ለመልካም የሚለውጥለት እንደ እኛ አይነት ህዝብ የለም፡፡
በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ ፊልጵስዩስ 2፡14-15
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10
  • · ለጥላቻ አልተጠራንም
ይቅር ለማለት ለመፍታት ለመባረክ ለማንሳት ለመጥቀም እንጂ ማንም ሰው ለመጥላት አልተጠራንም፡፡ እግዚአብሄር እንደ እኛ ምህረት ያደረገለት ሰው የለም፡፡ ታላቅ ምህረት ያደረገልን እግዚአብሄር እኛም በተራችን ለሚበድሉን ሰዎች ምህረት እንድናደርግ ይጠብቅብናል፡፡ ሰውን ይቅር እንዳንል ፣ በምሬት እንድንኖርና ሰውን እንድንጠላ አልተፈጠርንም፡፡
ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። ዘሌዋውያን 19፡17
ሌሎቹንም ያልጠራንን ነገሮች እርስዎም ይጨምሩበት
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጥላቻ #ማጉረምረም #ቅናት #ሃሜት #ፉክክር #ማሰናከያ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment