Popular Posts

Wednesday, November 2, 2016

ጭንቀት የህይወት ጠር

ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ ማቴዎስ 6፡25-28
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6
ጭንቀት የሁላችንም የህይወት ተግዳሮት ነው፡፡ ሰው ሆኖ ለመጨነቅ አልፈተንም የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡ ጭንቀት ፊት ከሰጠነው ህይወታችንን የሚበላ አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ ጭንቀት እህህ ብለን ካስተናገድነው እስርስር የሚያደርግ አፍራሽ ሃይል ያለው መርዝ ነው፡፡
ሰው ሲጨነቅ በተለምዶ ማድረግ የሚችለውን ነገር ማድረግ ያቅተዋል፡፡ እንዳንዴ የሚያስፈልገን የምንጨነቅለትን ነገር ማግኘት ሳይሆን አለመጨነቅና በጌታ ላይ ማረፍ ብቻ ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ አትጨነቁ ብሎ በመከረን ፣ ባዘዘንና ባስጠነቀቀን ቁጥር ሁሉ የሚሰጠን ምክኒያት እግዚአብሄር ለእናንተ ያስባልና የሚል ነው፡፡ መጨነቅ የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት የመሞከር ትምክት ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት የምንሞክረው ደግሞ የራሳችንን ድርሻ ጥለን ነው፡፡ የእግዚአብሄን ድርሻ ለመስራት መሞከር ደግሞ ከንቱ ድካምና ብክነት ነው፡፡ ስለዚህ ነው በጭንቀት ምንም መለወጥ እንደማንችል መፅሃፍ ቅዱስ ደግሞ ደጋግሞ የሚያሳስበን፡፡ እኛ ግን ስንጨነቅ ስራ የሰራን ይመስለናል፡፡ ስንጨነቅ እድገት ያመጣን ስለሚመስለን በጭንቀታችን በከንቱ እንፅናናለን፡፡
ስንጨነቅ እየተለወጥን ይመስለናል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ስንጨነቅ ማደግ እናቆማለን፡፡ ስንጨነቅ የስራ ጉልበታችን እናባክናለን፡፡ ስንጨነቅ ህይወታችን መለወጡን ያቆማል ህይወታችን እየቀጨጨ ይሄዳል፡፡
የምናድገውና የምንለወጠው መጨነቅ አቁመን ጉልበታችንን እግዚአብሄን መፈለግ ላይ ስናውለው ብቻ ነው፡፡ የምንለወጠው ጉልበታችንን ፅድቁንና መንግስቱን በመፈለግ ላይ ስናውለው ብቻ ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ማረፍ #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment