እግዚአብሄርን መምሰል ወይም መንፈሳዊ ባህሪ ከእግዚአብሄር ጋር ኖረንና ቃሉን ታዘን በትእግስት በህይወታችን የምንገነባው በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ትክክለኛ የትጋታችን ውጤት የባህሪያችን መሰራት ነው እንጂ በህይወታችን ያለው ስጦታ እንዳልሆነ መፅሃፍ ቅዱሳችን ያስተምረናል፡፡
ባህሪያችን የራሳችን መንፈስ ፍሬ ነው፡፡ ስጦታ ግን ሰጭው እንደ ወደደ የሚሰጠንና የምንቀበለው ነገር ነው፡፡ ባህሪያችን እንደ ዛፍ ፍሬ ሲሆን ከችግኝነት ጀምሮ አድጎ ተጠብቆ በትጋት የሚያፈራ ሃብት ነው፡፡ ስጦታ ግን የገና ዛፍ ላይ እንደሚንጠለጠር ከረሜላ እና ቸኮላት ነው፡፡
በእርግጥም ደግሞ የሰውን ብስለት የሚናገርው ባህሪው እንጂ ስጦታው አይደለም፡፡ የሰውን መስዋእትነት ፣ መታዘዙን ፣ የሰውን ለጌታ መሰጠት የሚናገረው ባህሪ እንጂ ስጦታ አይደለም፡፡
ስጦታችን እንደ ድግስ ቤት ምግብ ሲሆን ባህሪያችን ግን የራሳችንን ሙያ ማደግ የሚያሳይ ሽንኩርት ከመክተፍ ጀምረን በቤታችን የምናበስለው ምግብን ይመስላል፡፡ የድግስ ቤት ምግብ የእኛን ታማኝነትና ትጋት የማይጠይቅ የሌላ ሰውና ጊዜያዊ ስጦታ ነው፡፡ የራሳችን የምግብ ሙያ ግን በፈለግን ጊዜ የምንጠቀምበት ሁሌ አብሮን የሚኖር የራሳችን ሃብት ነው፡፡ እግዚአብሄር ስጦታን ለመስጠት ሰከንድ አይፈጅበትም፡፡ ስጦታውን እንደ እግዚአብሄር ልብ በትክክል የምናስተዳድርበትን ባህሪያችን ለመሰራት ግን ወራትና አመታት ይፈጅብናል፡፡
ከሃብቱ ይልቅ ባህሪው ስለሚበልጥ ጌታ ሃብቱን ከመስጠቱ በፊት አስተዳዳሪውን ለመስራት ይፈልጋል፡፡ ሃብቱን የሚያስተዳድረውንም ሰው ለመስራት እና ለመቅረፅ እግዚአብሄር ጊዜ ወስዶ ይተጋል፡፡
- ከምቾታችን ይልቅ የባህሪያችን መሰራት ይበልጣል እግዚአብሄር እምነታችን እንዲፈተን የሚፈቅደው መከራው እኛን ስለማያገኘንና እግዚአብሄርን የሚያሳዝነውን የስጋችንን ባህሪ ከእኛ ለማስወገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር በመከራ ውስጥ እንድንታገስ የሚፈልገው በባህሪ ሙሉ ሰዎች እንድንሆን ለማድረግ ነው፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ያዕቆብ 1፡2-4
ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ ሮሜ 5፡3-4
- ከሃብታችን ይልቅ ባህሪያችን ይበልጣል እግዚአብሄር ሃብታችንን ከመጨመሩ በፊት በታማኝነት ማደጋችንን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ በታማኝነት ባደግን መጠን ሃብታችን ይበዛል፡፡
ሃብቱን የሚሸከመው ልባችን ካልሰፋና በባህሪ ካላደግን በስተቀር ሃብቱም ቢመጣም ሃብቱን የምንይዝበት ልቡ ስለሚጎድለን ፈጥኖ ይበተናል፡፡ ዘይቱን የሚይዘው ገንቦ ቀዳዳው ካልተደፈነ የሚቀመጥበት ዘይት ፈስሶ ያልቃል፡፡ ለሚፈለገውም አላማ መዋል አይችልም፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም። ምሳሌ 20፡21
- ከስጦታችን ይልቅ በባህሪ ማደጋችን ይበልጣል
ምንም ድንቅ ስጦታ ቢኖረን በፍቅር መነሻ ሃሳብ /ሞቲቭ/ ካላደረግነው አይጠቅምም፡፡ ምንም አገልግሎት ቢኖረን በፍቅር ካልተመራ ለትክክለኛው አላማ መዋል አይችልም፡፡
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡1-3፣13
- ከውጭ ውበታችን ይልቅ የባህሪያችን ውበት ይበልጣል
የውጭው ውበታችን ጊዜያዊ ነው፡፡ የውስጥ ውበታችን ግን ዋጋው እጅግ የከበረና ዘላቂ ነው፡፡
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment