Popular Posts

Follow by Email

Thursday, November 10, 2016

በአሜሪካ የሚገኙ ሁሉ ሊያነቡት የሚገባ

ዶናልድ ትራምፕ በነበረው የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ከውጭ አገር መጥተው በአሜሪካ የሚኖሩትን ስደተኞች አንደሚያባርር ቃል ሲገባ ቆይቷል፡፡
የተወዳዳሪው ንግግር የምረጡኝ ዘመቻ ስልትና የምርጫ ድምፅ ለማግኘት የተደረገ ነው እንጂ ከውጭ አገር የመጡትን ለማባረር አይችልም የሚሉ አስተያየቶችም ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ህጉን ሊያጠነክረውና በሰዎች ወደ አሜሪካ መፍለስ ላይ ተፅእኖ ሊያደርግ ይችላል ይላሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ የእግዚአብሄር ሃሳብ ምንድነው የሚለውን ማየት ይገባል፡፡
የፈጠረንና የሰራን እግዚአብሄር ነው፡፡ የምንኖረውም ለእርሱ ክብር ነው፡፡ በተለያየ ምክኒያት ሃገር ብንለውጥም እንኳን እግዚአብሄር በርን ካልከፈተ ወዴትም ንቅንቅ ማለት አንችልም ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሃገር ቤት እንዲኖሩ የፈለጋቸው ሰዎች ምንም ቢጥሩ የትም መሄድ አልቻሉም፡፡
አንዳንዳዶቻችን ደግሞ ባላሰብነው ሁኔታ አገር ለውጠናል፡፡ በምድር ላይ የተቀደሰም የተረገመም አገር የለም፡፡ ሁሉም የእግዚአብሄር ነው፡፡
የምድር ባለቤት እግዚአብሄር ነው፡፡ ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሄር ናት፡፡ ምድር ሁሉ የእግዚአብሄር ናት፡፡
ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት: ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ መዝሙር 24፡4
ስለምድር ባለቤትነት መፅሃፍ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። 1ኛ ሳሙኤል 2፡3፣8
በአሜሪካ የተወለደው ዜግነቴ አሜሪካዊ ነው ቢልም ምንም የሚያስመካ ነገር የለም፡፡ እርሱን አሜሪካ እንዲወለድ እግዚአብሄር እንዳደረገው ሁሉ አሜሪካ የሚኖሩትንም ኢትዮጲያዊያን በዚያ ምድር እንዲኖሩ ፈቅዷል፡፡ እግዚአብሄር የሚከፍተውን የሚዘጋ እንደሌለ የሚዘጋውን የሚከፍት ማንም እንደሌለ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡
በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል። ራእይ 3፡7
እግዚአብሄር ከተወለድንበት ምድር ወደሌላ ምድር ሲወስደን በምክኒያት ነው፡፡ እኛ ህይወታችንን ለመለወጥ ፣ ዘማዶቻችን እዚያ ስለሚኖሩ ፣ ለትምህርት ፣ ለተሻለ ስራ ለመሳሰሉት መጥተን ይሆናል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሄር ካልፈቀደው የሚሆን ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው እገዚአብሄር የዘጋውን ማንም ሊከፍተው አይችልምና፡፡
ስለዚህ በአሜሪካ የምትኖሩ ሁላችሁ ህዝቡ ወደደም አልወደደም እግዚአብሄር ካለ ትኖራላችሁ፡፡ መሪው ወደደም ጠላም ትኖራላችሁ፡፡ እግዚአብሄር ካልፈቀደላቸው በስተቀር ሰዎች ጠልተዋችሁ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ የእነርሱንም ጨምሮ የሁላችንንም እስትንፋስ የያዘው ጌታ እግዚአብሄር ነው፡፡
ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፤ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መዝሙር 104፡29
እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም። ምሳሌ 26፡2
በምድር ተቀመጥ ታምነህ ተሰማራ የሚለው ምክር ለሁላችንንም ይጠቅመናል፡፡ በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። መዝሙር 37፡3
ማንንም አትፍሩ ይልቁንስ እግዚአብሄርን ፍሩ፡፡ ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡14-15 ሁላችንም እንደዚህ እንበል፡፡
እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? መዝሙር 118፡6
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ያድርጉ! ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አትፍራ #ታመን #መሪ

No comments:

Post a Comment