Popular Posts

Thursday, November 3, 2016

የሰይጣን ማታለያ መንገዶች

በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡11
ሰይጣን የሚመጣው ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ ነው፡፡ ሰይጣን ከዚህ ሌላ አላማና ተልእኮ የለውም፡፡ ሰይጣን ከመጣ ለመስረቅ ለማረድና ለማጥፋት ብቻ ነው፡፡ ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ ዮሃንስ 10፡10
ይህንንም የሚያደርገው በግድ አይደለም፡፡ በጌታ ተከታዮች ላይ ስልጣን ስለሌለው ይህን የሚያደርገው በግልፅ አይደለም፡፡ ሰይጣን አላማውን ከፈፀመብን የሚያደርገው በማታለልና በአለማወቃችን በመጠቀም ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሃዋሪያው የሰይጣንን ሃሳብ አንስተውም የሚለው፡፡
ሰይጣን በእኛ ላይ ሃይል የሚያገኝበት ብቸኛው መንገድ ለእግዚአብሄር ያለንን የዋህነት በማበላሸት ነው፡፡ ሃሳባችን ከተበላሸ እግዚአብሔርን ማመን እንተዋለን፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ላይ መዝራትን እናቆማለን፡፡ የተፈጠርንበትን አላማ እንስተዋለን ከዚያ ይልቅ የመብላትና የመጠጣት ተራ ጥያቄ በመፍታት ህይወታችንን እናባክናለን ከንቱ ሰዎችም ሆነን እንቀራለን፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡3
ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልልበትና የሚያስትበት ሃሳቦችን እንመልከት፡፡
  • · ክፍፍልና ፉክክር
እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ የተጠራው ለተለየ አገልግሎት ነው፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶች ግን በአንድ ላይ ለአንድ መንግስት ይሰራሉ፡፡ ለአንድ መንግስት እንደማይሰራ ሰይጣን ካሳመነን ተታለናል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መንግስት ከሌላው ሰራተኛ ጋር በመተባበር እንጂ በመፎካከር መስራት ከጀመረ የሰይጣን ሃሳብ አግኝቶታል ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።ሮሜ 12፡3-5
  • · ይቅር አለማለት
ይቅር የማይል ምህረት የሌለው መራርና የጥላቻ ልብ የሰይጣን ለም መሬት ነው፡፡ ሰይጣን ሰውን እንዲጠላ ካደረገው እንዲገድል አድርጎታል ማለት ነው፡፡ ጥላቻና ግድያ አንድ ናቸውና፡፡ ሰይጣን ሰዎችን መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ጥላቻ የሌለባቸውን ሰዎች ግን በመጠቀም የመግደል አላማውን ሊያሳካ አይችልም፡፡
እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡10-11
  • · የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል
በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። ማርቆስ 4፡18-19
በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 8፡14
የኑሮ ጭንቀት አሳስሮ የሚያስቀምጠን አደገኛ የሰይጣን መሳሪያ ነው፡፡ የኑሮ ጭንቀት ከአላማችን በማስቆም የኑሮን ጥያቄ ብቻ እየመለስን እንደማንኛውም አህዛብ ተራ ሰው ሆነን እንድኖር የሚያደርገን የሰይጣን ማታለያ መንገድ ነው፡፡
የኑሮ ስጋት በእግዚአብሄር ላይ ብቻ እንዳንደገፍ ለጌታም ለገንዘብም ለመገዛት እንድንሞክር የሚያደርግበት የሰይጣን ማታለያ ነው፡፡ የባለጠግነት ምኞት ጌታን ከማገልገል እንድናፈገፍግ የሚያደርግበት የሰይጣን ማታለል ነው፡፡ በመጠኑ እንዳንኖር ፣ በኑሮዋችን እንዳንረካ እና ለቤተክርስቲያን በረከት እንዳይሆን ጉድለታችንን ራቁታችንን ካሳየን በሰይጣን ተታለናል ማለት ነው፡፡
  • · ትዕቢት
ይህ ደግሞ ሰይጣን ራሱ የወደቀበት መንገድ በመሆኑ የሰይጣን መጣያና ከእግዚአብሄር መንግስት ሩጫ የሚያስወጣበት ስልት ነው፡፡ ከእኛ በላይ እንደሌለ እኛን ሊናገረን ሊያርመንና ተጠያቂ ልንሆንለት የሚገባ ማንም ሰው እንደሌለ በትእቢት ማሰብ ስንጀምር በሰይጣን ማታለል ስር እንደሆንን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ሌላውን መስማትና ለሌሎች መገዛት ካቃተን ሰይጣን አስቶናል ማለት ነው፡፡ ሰይጣን በትእቢት እንድናስብ ካደረገን የሰይጣንን ማታለል ተታለናል ማለት ነው፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።1ኛ ጴጥሮስ 5፡5
በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ዲያቢሎስ #ጠላት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ማታለል #የተሸነፈ #በረከት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment