እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ማቴዎስ 6፡31-32
ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን ለኑሮ እንዳንጨነቅ ኢየሱስ ደጋግሞ ደጋግሞ ያስተምረናል፡፡ ስለኑሮ መጨነቅ የእናንተ አይደለም እያለን ነው፡፡ ለኑሮ መጨነቅ አይመጥናችሁም እያለን ነው፡፡ ስለኑሮ መጨነቅ ክብራችሁ አይፈቅደውም እያለንም ነው፡፡
ስለኑሮ መጨነቅንና ለመኖር መኖርን እንደትልቅ ነገር አይተውት የሚኖሩለትና የሚሞቱለት ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለመኖር ነው የሚኖሩትና የሚሰሩት፡፡ እነዚህ ሰዎች ለመኖር የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ከመኖር ውጭ የሚኖሩለት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች መኖር የሙሉ ጊዜ ሃላፊነት ነው፡፡
ህይወታቸውን ሁሉ የሰጡት ለመኖር የሚያስፈልገውን በማሟላት ነው፡፡ የሚኖሩለት የእግዚአብሄር ጥሪ በህይወታቸው ላይ የለም፡፡ እግዚአብሄር ለህይወታቸው ያስቀመጠውን የተለየ አላማ አላገኙትም፡፡ ስለሚበላና ስለሚለበስ ከመጨነቅ የተሻለ ስራ የላቸውም፡፡
ስለኑሮ መጨነቅ እግዚአብሄርን የማያውቁ የተሻለ የህይወት አላማ የሌላቸው ሰዎች የህይወት ዘይቤ እንደሆነ ኢየሱስ ያስተምራል፡፡ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ማቴዎስ 6፡32
ለመኖር የሚጨነቁት ሌላ ምንም ሃላፊነት የሌለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ለመኖር የሚጨነቁት ሌላ የተሻለ የሚኖሩለት የህይወት ራእይ ስለሌላቸው ነው፡፡ ለመኖር የሚጨነቁት በህይወታቸው የሚከተሉት የእግዚአብሄር አላማ በህይወታቸው የሌላቸው ናቸው፡፡ እነዚያ ለመኖር የሚጨነቁት መንገዱ የጠፋባቸውና እግዚአብሄር ለከበረ የህይወት አላማ እግዚአብሄርን ለማምለክና ለማገልገል እንደጠራቸው የማያውቁ ናቸው፡፡ ስለኑሮ የሚጨነቁት የሚፈልጉት የእግዚአብሄር መንግስት ስሌላቸው ነው፡፡ እነዚህ ስለሚበላና ስለሚጠጣ የሚጨነቁት የሚፈልጉት የእግዚአብሄር ፅድቅ ስለሌላቸው ነው፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
ኑሮን ዋና የህይወት አላማ ያደረጉት ናቸው ስለመኖር ብለው የሚኖሩት፡፡ እነዚህ ሰዎች ህይወታቸውን ሁሉ የሚጨርሱት ለመኖር በመጨነቅ ለመኖር በመሞከር ብቻ ነው፡፡ እንደው ከመኖር የተሻለ ምንም የሚከተሉት የህይወት አላማ የላቸውም፡፡ የመጨረሻውና ታላቁ ግባቸው መኖር ነው፡፡
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡19
ለእነርሱ መኖር ብቻውን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለእነርሱ እግዚአብሄር ሊሰሩት ያዘጋጀውን መልካሙን ስራ መስራት ሳይሆን ኖሮ ኖሮ መሞት ትልቅ ገድል ነው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ኢየሱስ ስለኑሮ አትኑሩ ለመንግስቴ ኑሩ እያለን ነው፡፡ ፅድቅን ለማሳየት ስትኖሩ ይህ ሁሉ ነገር ምርቃት ነው እያለን ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ማቴዎስ 6፡31-32
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #ህልም #አላማ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment