የጠላት ዲያቢሎስ አላማ ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት አይዘልም፡፡ ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሐንስ 10፡10
የህይወት ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያቢሎስ ከሚታወቅባቸው ስሞቹ አንዱ የውሸት አባት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ሰይጣን ይዋሻል፡፡ ሰይጣን በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለተሸነፈና ስልጣኑን ስለአጣ አሁን የቀረው መሳሪያ መዋሸትና ማታለል ብቻ ነው፡፡
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሐንስ 8፡44
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3
ሰይጣን የሚዋሸው በእግዚአብሄር ቃል ላይ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በውስጣችን ከሌለ ሊያሳስተን ሁሌ ይመጣል፡፡ ሰዎች ይህን የሰይጣንን ውሸት ሲያምኑ በዚህም ህይወታቸው ሲበላሽ እናያለን፡፡ ሰይጣን እንዴት እንደሚዋሽ እንመልከት
- · እየጠፋህ ነው ዋጋ የለህም ትወድቃለህ ካለህ የሰይጣን ማታለል መሆኑን አውቀህ በእግዚአብሄር ቃል ፀንተህ ተቃወመው፡፡ ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። ምሳሌ 4፡18
- · ሰይጣን በሃጢያት ውስጥ ደስታ ይገኛል አለምህን ቅጭ እንጂ ለምን ጊዜ ያልፍብሃል? ካለ ሰይጣን እየዋሸህ ነው፡፡ በአለም የቀረብህ ነገር ቢኖር አሳፋሪ ፣ ፍሬቢስና መጨረሻው ሞት የሆነ ነገር ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። ሮሜ 6፡21
ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። ዕብራውያን 11፡25-26
- · ሃብታም የሆነው ሰው ሁሉ ሃብት ያገኘው በማጭበርበር ነው ካለ አንተም ካላጭበረበርክ መበልፀግ አትችልም ስለዚህ አጭበርብር እያለህ ነው፡፡ ይህ የሰይጣን ድምፅ ነው፡፡ ሰው በታማኝነት በእግዚአብሄር ሊበለፅግ ይችላል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
- · እግዚአብሄር ለአንተ ግድ የለውም እራስህን አድን ፡፡ እግዚአብሄርን አትጠብቅ የራስህን መንገድ ሂድ የሚለው ድምፅ የሰይጣን ድምፅ ነው፡፡ ሰይጣን ሄዋንንም ተመሳሳይ ነገር ብሎዋት ነበር፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
- · ማንንም አታገልግል ሰዎች ይጠቀሙብሃል ፡፡ ስለዚህ ከቤተክርስቲያን ሽሽ አምልጥ የሚልህ ሰይጣን ሲሆን ለምታገለግለው ለእግዚአብሄር ያለህን አመለካከት እያበላሸ ነው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ማቴዎስ 25፡24-26
- · ሌላው ሰው አያስፈልግህም አንተ ብቻ በቂ ነህ ከአለህ ሰይጣን በትእቢት ሊጥልህ እያናገረህ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
- · ካልተጨነቅህ ጤነኛ ሰው አይደለህም፡፡ አለመጨነቅ አይቻልም የሚለው የጠላት ድምፅ ነው፡፡ አንተ በቂ ጭንቀት አለህ እግዚአብሄርን ማምለክና ማገልገል የምትለውን ነገር ትተህ ለኑሮህ በመጨነቅ ህይወትህን ግፋ የሚለው ሰይጣን ዲያቢሎስ ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
- · አንተ ምስኪን ነህ ለእግዚአብሄር የምትሰጠው ምንም ነገር የለህም የሚለው ሰይጣን ለብዙዎች በረከት እንዳትሆን ሊያደርግ ነው፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡10
- · ለማንም ቤተክርስቲያን አትገዛ ፣ በየትኛውም ስልጣን ስር አትሁን ፣ በግልህ ኑር አገልግል ካለህ ሰይጣን ነው፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5
- · አንተ ብቻ ነህ በመከራ ውስጥ የምታልፈው ካለአንተ በስተቀር ሰው ሁሉ ኑሮ ቀሎለት እየኖረ ነው ካለህ ይህ ንግግር ከሰይጣን እንደሆነ እወቅበት፡፡ ሰይጣን ሁሉም ሰው ጋር እየሄደ እንደዚያ ነው የሚለው፡፡
በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8-9
- · አንተ በሃጢያት ከመውደቅ አልፈሃል ምንም መጠንቀቅ የለብህም ካለህ ይህ ሃሳብ ከሰይጣን ነው፡፡
ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡12
- · በእኔ ላይ የደረሰው ከምችለው ከአቅሜ በላይ ነው፡፡ ከዚህ የምወጣበት ምንም መንገድ የለም ካልክ የሰይጣንን ንግግር አምነሃል ማለት ነው፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ውሸት #ሀሰት #ሰይጣን #ዲያቢሎስ #ጠላት #ማታለል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment