አንድ ቤቶችን እየሰራ የሚሸጥና የሚያከራይ ባለሃብት ነበረ፡፡ ለባለሃብቱ ቤቶችን የሚገነባለት ሁነኛ አናፂ ነበረው፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ እያነፀለት ሲኖር ቆይቶ እድሜው እየገፋ ስለመጣ ጡረታ መውጣት ፈለገ፡፡
አናፂው ከስራው እንዲያሰባብተው ባለሃብቱን ጠየቀው፡፡ ባለሃብቱ ግን በጣም ጥሩ አድርጎ የሚሰራለት ታማኝና ትጉህ አናፂ ስለነበረ ጡረታ እንዳይወጣ ነገር ግን እንዲሰራለት ሃሳቡን ለማስቀየር አጥብቆ ለመነው፡፡
አናፂው ግን ልቡ ስለተነሳ በፍፁም በስራው ለመቀጠል ፈቃደኛ ሊሆንለት አልቻለም፡፡ ሊያስቀረው የጣረው ጥረት እንዳልተሳካ ያየው ባለሃብት እሺ እለቅሃለሁ ከመውጣትህ በፊት ግን አንድ የመጨረሻ ቤት ስራልኝ ብሎ ለመነው፡፡
አናፂው በሃሳቡ ተስማማ፡፡ ነገር ግን ልቡ ወጥቶ ስለነበር ጥራት በሌለው እቃ እንደ ነገሩ አድርጎ ቶሎ ሰርቶ ቤቱ አስረከበው፡፡አሰሪውም ለረጅም አመታት በታማኝነትና በትጋት ስላገለገልከኝ ይህ ቤት ለአንተ ስጦታ ነው ብሎ የመጨረሻውን ቤት በደስታ አስረከበው፡፡ አናፂው ግን ከደስታ ይልቅ በጣመ አዘነ ተፀፀተም፡፡ ጥራቱን ባልጠበቀ እቃ ፣ በችኮላ የይድረስ ይድረስ ውትፍ ውትፍ አድርጎ ስለሰራው በጣም ተቆጨ፡፡
አናፂው የራሱን ቤት እንደሚሰራ ቢያውቅ ኖሮ እንዴት በተሻለ ጥራት በጥንቃቄ ይሰራው ነበር?
እንዲሁ እያንዳንዳችን የምንሰራው የራሳችንን ቤት ነው፡፡ ነገ የምንኖረው ዛሬ በሃሳባችን ፣ ንግግራችንና በድርጊታችን በምንሰራው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ በምንሰራው ቤት ውስጥ ነው ልጆቻችን የልጅ ልጆቻችንና ትውልዳችን የሚኖረው፡፡
ስለዚህ በእያንዳንዷ ደቂቃና ሰአት የወደፊት ቤታችንንና ትውልዳችንን እንዴት እንደምንሰራ እንጠንቀቅ፡፡ ይህ እንዲህ ከሚለው ከእግዚአብሄር ቃል ጋር ይስማማል፡፡
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። ገላትያ 6፡7-9
እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ሉቃስ 16፡11-12
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ታማኝ #ትጉህ #ቤት #ትውልድ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ሃሳብ #መናገር #ድርጊት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment