Popular Posts

Thursday, September 8, 2016

የድህነት ብፅዕና


በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ማቴዎስ 5፡3
ልጆች ጣፋጭ ነገር ይወዳሉ፡፡ ስለዚህ ጣፋጭ ነገር ካገኙ መብላታቸውን ብቻ ነው የሚያስቡት፡፡ ጣፋጭ ነገር ብዙ ከበሉ ደግሞ የምግብ ፍላጎታቸው ይቀንሳል፡፡ ልጆች ዝም ከተባሉ የትኛው ይበልጥ እንደሚጠቅማቸው ስለማያስተውሉ ይጎዳሉ፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሰዎች ለዘላለማዊ ህይወት የማይጠቅም ከተሰሩበት ንድፍና እቅድ ጋር የማይሄድ ነገር ጋር ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በማፍሰስ ህይወታቸውን ያባክናሉ፡፡ ለመንፈሳ ነገር ምንም በማይጠቅም ምድራዊ ነገር ላይ በማተኮር ክቡር ህይወታቸውን ያባክናሉ፡፡
እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ኢሳይያስ 55፡1-2
በመንፈስ ድሆች የሆኑ መንፈሳቸውን እግዚአብሄር እንጂ ሌላ ቁስ ሊያረካው እንዳማይችል የተቀበሉ ሰዎች የተባረኩ ናቸው፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
በመንፈስ ድሆች የሆኑ በሁለንተናቸው የእግዚአብሄር እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እውቅና የሚሰጡ ሰዎች ብፁአን ናቸው፡፡
ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ዮሃንስ 15፡5 በመንፈስ ድሆች የሆኑ እግዚአብሄር ብቻ ሊሞላው የሚችለውን በውስጣቸው ያለውን ጉድለት የተረዱ ብፁአን ናቸው፡፡
ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው? መክብብ 2፡25
በመንፈስ ድሆች የሆኑ ያለውን አምላክን ለማምለክ በውስጣቸው ያለውን ጩኸት የተረዱ እውነተኛውን አምላክ የሚፈልጉ ብፁአን ናቸው፡፡ እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። ዮሃንስ 17፡3
በመንፈስ ድሆች የሆኑ ካለእግዚአብሄ ምንም እንዳልሆኑ የተረዱ ብፁአን ናቸው፡፡
እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። መዝሙር 16፡2
በመንፈስ ድሆች የሆኑ ከእግዚአብሄር ውጭ ህይወት ከንቱ እንደሆነ የተረዱና እግዚአብሄርን ማምለክ ብቻ የሚያረካቸው ከዚያ ውጭ ምንም የማያረካቸው ብፁአን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡
እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ። መዝሙር 17፡15
በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ማቴዎስ 5፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum...

No comments:

Post a Comment