ሰው ሁሉ ሃጢያትን ሰርቶ ከእግዚአብሄር ክብር ስለወደቀ ንስሃ ገብቶ ከእግዚአበሄር ጋር መታረቅ አለበት፡፡ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለሃጢያቱ የሰራውን ስራ ለእኔ ነው ኢየሱስ የሞተው በእኔ ምትክ ነው ብሎ የሚቀበል ሰው እግዚአብሄር ይቀበለዋል በቤተሰቡ ውስጥ ልጅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የአባትና የልጅ ግንኙነት ይኖረዋል እግዚአብሄርን በግሉ ያውቀዋል፡፡
የኢየሱስ ከሃጢያት አዳኝነት የምስራች ሲበሰርላቸው ብዙ ሰዎች እኔ ክርስቲያን ነኝ ብለው ስለሚያስቡ ብቻ ኢየሱስን ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ነገር ግን ክርስትናን እንደማንኛውም ሃይማኖት ሃይማኖቴ ነው ብሎ የያዘ ሰው ሁሉ ድኗል ማለት አይቻልም፡፡ እየሱስ ወደምድር የመጣው አንድ ተጨማሪ ሃይማኖት ለመመስረት ሳይሆን ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር እንዲታረቁና የአባትና የልጅ ግንኙነት አንዲኖራቸው ነው፡፡
ክርስትና ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሄር ጋር የግል ግንኙነት መመስረት ነው፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ግንኙነት እንዳለንና እንደሌለን 5 መመዘኛዎች
· ህይወታችን በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን የመጨረሻው ስልጣን ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄ ቃል አድርጉ የሚለንን እናደርጋለን አታድርጉ የሚለንን አናደርግም፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12
· እግዚአብሄርን በሰሚ ሰሚ ሳይሆን በግላችን እናውቀዋለን፡፡ እግዚአብሄርን በእለት ተእለት ህይወታችን እንፈልገዋለን በህይወታችን በእያንዳንዱ የህይወት ክፍላችን ሲሰራ እናውቀዋለን፡፡
ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ 1ኛ ዮሐንስ 1፡1-2
· ከእግዚአብሄር ጋር በየእለቱ እንነጋገራለን፡፡ እግዚአብሄርን የምናውቀው በታሪክ ወይም በሰዎች ልምምድ ሳይሆን የእግዚአብሄርን አባትነት በህይወታችን እንለማመዳለን፡፡ እንደ አባት እንጠራዋለን እንደ ልጅ ይሰማናል ይናገረናል፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
· በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከማንም ከምንም አብልጠን ኢየሱስን እንከተላለንሽሽ የኢየሱስን አስተምሮዎች ሁሉ እንታዘዛለን፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ማቴዎስ 28፡19-20
· ኢየሱስ በልባችን ይኖራል፡፡ ክርስትና ሃይማኖታዊ ወግና ስርአት መፈፀም ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሄር መኖርና በእግዚአብሄር ሃይል ማገልገል ነው፡፡ ኢየሱስን የምናውቀው በልባችን ሲኖርና ከልባችን ሲመራንና በልባችን በመኖር ሃይል ሲሰጠን ነው እንዲያውም ኢየሱስ በእኛ ሲወጣና ሲገባ ስራውን ሲሰራ ነው፡፡
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum...
No comments:
Post a Comment