ከእግዚአብሄር ጋር የኖሩ ሰዎች ሁሉ እግዚአብሄር ባሳለፋቸው ጎዳና ሁሉም "ግን ለምን?" ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ከእኛ ሙሉ መታመን የሚጠብቀው እግዚአብሄር "ጌታ ሆይ እኔን ለምን?" የሚለውን ጥያቄ ሁልጊዜ አይመልስም፡፡
ኢዮብ የራሱን ንፅህና ተመልክቶ ተማምኖዋል፡፡ የሚያልፍበት ሁኔታ ደግሞ በጥንቃቄ ለጌታ ለሚኖር ሰው እንደማይገባ አሰበ፡፡ እግዚአብሄርን ፊት ለፊት ባገኘው በክርክር እረታው ነበር ብሎ እስከ መናገር ደርሶዋል፡፡
እግዚአብሄርን መከተል እንደ ጥቁርና ነጭ ሁሉንም ነገር ብጥር አድርገን አውቀነው የምንከተለው ሳይሆን ባወቅነው እውቀት እየኖርን ባልተረዳነው ነገር ደግሞ በእግአዚአብሄር ላይ እየተደገፍን የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን የሚሰራውመን ስራ ሁሉ ምክኒያቱን ለመረዳት እንደ እግዚአብሄር ሁሉን አዋቂ መሆን አለብን፡፡ ሁሉንም እንደማናውቅ በመረዳት እርፍ ማለት ትህትና ነው፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር የኖሩ ሰዎች ሁሉ እግዚአብሄርን ተረድተውት ጨርሰው አይደለም፡፡ የተገለጠላቸው እውነት ይበቃል ብለው ባልተረዱት ነገር በእግዚአብሄር ላይ ተደግፈው ነው፡፡ እግዚአብሄርን የተረዱት በትህትና እንዲህ ይላሉ፡፡
ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው። ዘዳግም 29፡29
እግዚአብሄር ለምን እኔን ግን የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ለነበረው ለኢዮብ በቀጥታ አይደለም የመለሰው፡፡ አነጋገርህ ስራዬን ሁሉ ልቅም አድርገንህ የምትረዳ ነው የምትመስለው ነገር ግን ፍጥረትን ስፈጥር የት ነበርክ ነው ያለው፡፡ ሁሉን እንደሚያውቅ ነው የምትናገረው ምድርን ስሰራ አንተ የት ነበርክ በማለት ነበር እግዚአብሄር የኢዮብን ጥያቄ በጥያቄ የመለሰው፡፡ ግን እኔን ለምን ለሚለው ሰው እግዚአብሄር ዛሬም ይናገራል፡፡
እግዚአብሄር እንዲህ ይላል ሁሉንም ስላማታውቅ በእኔ ላይ ብቻ ተደገፍብኝ፡፡ ሁሉንም ዘርዝረህ ለማወቅ መሞከር ትእቢት ነው፡፡ ስለዚህ ትህትናህን ጠብቅ እመነኝ ይላል እግዚአብሄር፡፡
ያቆብም እግዚአብሄር የሚሰራውን ነገር ስላልተረዳ እግዚአብሄር የመለሰውን ለራሳችን እንስማ፡፡
ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ 40፡27-28
መፍትሄው "ለምን እኔን?" የሚለውን የማይመለስ ጥያቄ ከመጠየቅ ይልቅ ሃይል የሚሰጥህ በእኔ ላይ መደገፍ ነው ይላል እግዚአብሄር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ማድረግ የምትችለው ብቸኛ መፍትሄ በእኔ መደገፍ ነው ይላል እግዚአብሄር፡፡ የሚሆነውን ሁሉ አልረዳም ትላለህ፡፡ ሁሉን እንደማታውቅ እኔም አውቃለሁ፡፡ ሁሉንም እንድትረዳም አልጠብቅም ይላል እግዚአብሄር፡፡ ሁሉም በማውቀው በእኔ ግን እንድትደገፍ እጠብቃለሁ ይላል እግዚአብሄር፡፡ ያንተ ድርሻ ሁሉንም ማወቅ ሳይሆን በማታውቀው በእኔ መታመን ነው ይላል እግዚአብሄር፡፡
ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳያስ 40፡29-31
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
#መታመን #እምነት #መደገፍ #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ
No comments:
Post a Comment