እግዚአብሔር በኢየሱስ የመስቀል ስራ ለወለዳቸው ልጆቹ ሁሉ ሁልጊዜ ይናገራል፡፡ በምድር ላይም ሁለት አይነት ድምፆች አሉ፡፡ ሰይጣንም እንዲሁ በስጋ አማካኝነት ይናገራል፡፡ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ድምፅ አለ፡፡ በምድር ላይ የስጋና የሰይጣን ድምፅ አለ፡፡ ሰይጣን የሚናገረው የስጋችንን ፍላጎት ተጠቅሞ ነው፡፡ የስጋችን ድምፅ የሰይጣንም ድምፅ ነው፡፡
ከድምፆች መካከል የእግዚአብሔር ድምፅን መለየት እግዚአብሔርን ብቻ እንድንታዘዝና እርሱ ወደ አዘጋጀልን የህይወት በረከት ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ ከሌሎቹ ከሰይጣንና ከስጋ ድምፅ የሚለይበት መንገድ
1. የእግዚአብሔር ድምፅ ሰላም ያለው ድምፅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ የሚያስጠነቅቅ ድምፅ አንኳን ቢሆን ከመፍትሄ ጋር ያለ ድምፅ ነው እንጂ የጭንቀት ድምፅ አይደለም፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና። መዝሙር 85፡8
2. የእግዚአብሔር ድምፅ የእረፍትና ገራገር /Gentle/ ድምፅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ የሚመራ ድምፅ አንጂ የሚነዳ ድምፅ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ ጊዜ ወስደን አንድናስብበት እውቀትን በመስጠት ለተሻለ ውሳኔ የሚያስታጥቅ ድምፅ እንጂ ግባ ግባ ካልገባህ ብሎ ካለ ፈቃዳችን እንድንወስን የሚያስጨንቅና በግድ የሚነዳ ድምፅ አይደለም፡፡
በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። መዝሙር 23፡2
3. የእግዚአብሔርን ድምፅ የምንሰማው በልባችን ነው፡፡ በአእምሮዋችን ጥርጥር እያለ በልባችን ግን የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት እንችላለን፡፡
ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ሆሴዕ 2፡16
4. የእግዚአብሔር ድምፅ በቀጣይነት የምንሰማው ድምፅ እንጂ በአንዴ እንደጎርፍ መጥቶ በድንገት አስወስኖን የሚሄድ የሚነዳ ድምፅ አይደለም፡፡
መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል። ኢሳይያስ 40፡11
5. የእግዚአብሔር ድምፅ በጊዜ ውስጥ እየጠራ እየጠነከረ የሚሄድ ድምፅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ የድምፅ ጎርፎች ካለፉ በኋላ ስክን ብሎ የሚንቆረቆር ድምፅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ አይለቅም እስከምንታዘዘው ይቆያል፡፡
እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ እንዲህም አለኝ፦ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፥ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና ስለዚህ፥ ኢሳይያስ 8፡5-6
6. የእግዚአብሔር ድምፅ ትክክለኛውን መንገድ በማሳየት ያበረታታል እንጂ በመኮነን ዝቅ ዝቅ አያደርግም አያጎሳቁልም ተስፋ የለህም ጠፍተሃል አይልም፡፡ እግዚአብሔርም፦ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። ዘጸአት 33፡14
7. የእግዚአብሔር ድምፅ የእግዚአብሔርም ቃል የሚያስታውስና በፍቅር እንድንኖር የሚያበረታታ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ ራስ ወዳድነታችንን አሳትይቶ ይበልጥ ለጌታ መስዋእት እንድናደርግ የሚያበረታታ ድምፅ ነው፡፡
ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። መዝሙር 23፡3
8. የእግዚአብሔር ድምፅ ተስፋን የሚሞላና ብሩህነትን በማሳየት የሚያፅናና ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ ደስታን የሚሞላ ምንም በሌለበት ደስ እንዲለን የሚያደርግ የደስታ አብሳሪ ነው፡፡
በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። መዝሙር 23፡4
9. የእግዚአብሔር ድምፅ በምናውቀው ላይ ተጨማሪ ብርሃንን በመስጠት እንድንወስን እንድንጨክን ያስታጥቃል አንጂ በጥርጥር ሁኔታውን በማጨለም ተስፋ አያስቆርጥም፡፡
የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ። ሮሜ 15፡13
10. የእግዚአብሔር ድምፅ በራሳችን ድካም ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር መልካምነትና ሃይል ላይ አንድናተኩር የሚያደርግ ድምፅ ነው፡፡
እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና። ማቴዎስ 11፡28-30
#እግዚአብሔር #አምላክ #ድምፅ #ምሪት #ሰላም #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment